የዋጋ ግሽበቱ በመጪዎቹ 6 ወራት ሁለት አሃዝ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ተናገረ።
- 1 hour ago
- 1 min read
ሐምሌ 6/2018
የዋጋ ግሽበቱ በመጪዎቹ 6 ወራት ሁለት አሃዝ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ተናገረ።
ይህን ለመቋቋም ያግዝ ዘንድም በባንኮች ላይ ተጥሎ የቆየው የብድር ገደብ ቢነሳም ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው እንዲቀጥል ተወስኗል ብሏል።
በባንኩ ስር የተቋቋመው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ሰባተኛውን ስብሰባ አካሂዶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የገንዘብ ኮሚቴው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም በዚህ አመት ታህሳስ ወር ላይ የዋጋ ግሽበት ወደ አንድ አሃዝ 9 ነጥብ 7 በመቶ ወርዶ እንደነበረ አስታውሰዋል።
ይሁንና የኢራኑን ጦርነት ተከትሎ የዋጋ ግሽበቱ ወደ ሁለት አሃዝ ከፋ ብሎ ባለፈው ሚያዝያ ወር 11.7 በግንቦት ወር ደግሞ ወደ 13. 4 በመቶ ከፍ ብሏል ብለዋል ዋና ገዥው፡፡
በመጪው ስድስት ወርም የግሽበት ምጣኔው ሁለት አሃዝ ሆኖ እንደሚቀጥል እና በታህሳስ ወር 2019 ዓ.ም ጀምሮ ሊቀንስ እንደሚችል የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ገምግሟል ተብሏል።
ይህን ለመቋቋም ያስችል ዘንድም ከሚቴ ው የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ዶ/ር እዮብ አክለዋል።
ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው እንዲቀጥል ኮሚቴው በሰባተኛው ስብሰባው ካሳለፋቸው መካከል ናቸው።
በባንኮች ላይ ተጥሎ የቆየው የብር ገደብ መነሳቱን የጠቀሱት ዋና ገዢው ይህ ግን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ለውጥ ሳይሆን ይሄንኑ ፖሊሲ ለማስቀጠል በፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ሁሉንም ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎችን መጠቀሙን ይቀጥላል ተብሏል።
ሌላ በኩል የገቢ ንግዱ የሚያስወጣውን ወጭ ለመቀነስ እና የዋጋ ግሽበት ላይ የሚኖረውን ተፅእኖ ለመቀነስ የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ኮሚሽን ምጣኔ ከ2.5 በመቶ ወደ 1.5 በመቶ እንዲቀንስ ተወስኗል ተብሏል።
ይህም ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ገበያ እንዲኖር እየከሆነ ያለውን ስራ ግብ እንዲመታ ማድረግ ነው ያሉት የባንኩ ዋና ገዥ የውጭ ምንዛሬ ጨረታውም እገዛ እያደረገ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ባንኮች እርስ በርስ ገንዘብ እንዲበዳደሩ በተዘረጋው አሰራር ከ3 ትሪሊየን ብር በላይ ተገልብጧል።
በመጭው አመት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ የሚገበያዩበትን ቴክኖሎጂ እዘረጋለሁ ብሏል ብሔራዊ ባንክ።
ትዕግስት ዘሪሁን

