የኮንትሮባንድ እቃዎች ጭኖ የተገኘተሽከርካሪ በመንግስት እንዲወረስ የሚያስገድድ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡
- 4 hours ago
- 2 min read
መጋቢት 15/2018
የኮንትሮባንድ እቃዎች ጭኖ የተገኘተሽከርካሪ በመንግስት እንዲወረስ የሚያስገድድ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡
እንደገና ተሻሽሎ ዛሬ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በቀረበው የጉምሩክ አዋጅ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ለማሳለፍ የሚሆን መደበቂያ ቦታ የተሰራለት ተሽከርካሪ ወይም ሙሉ በሙሉ የኮንትሮባንድ እቃ የጫነ መሆኑ ከተረጋገጠ መኪናው በመንግስት እንዲወረስ ተደንግጓል፡፡
ከሰባት አመት በፊት በፀደቀው የአዋጁ ማሻሻያ ተሽከርካሪዎች በኮንትሮባንድ ንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ቢገኙም ባለቤቶቹ በወንጀሉ ተሳታፊ ባልሆኑበት ሁኔታ ንብረታቸው እንዲወረስ መደረጉ ፍትሃዊ አይደለም በሚል 100 ሺህ ብር ቅጣት እንዲጣልባቸው ተደንግጎ እንደነበር ለፓርላማ የቀረበው የማሻሻያ አዋጁ ማብራሪያ ያስታውሳል፡፡
ይሁንና ኮንትሮባንዲስቶች ራሳቸው ይሄንኑ የ100 ሺህ ብር ቅጣት እየከፈሉ ህገ-ወጥ ንግዱ እየተጧጧፈ መሆኑ በመረጋገጡ ችግሩን ለመቅረፍ የኮንትሮባንድ እቃ ጭነው ከተገኙ ተሽከርካሪዎች እንዲወረሱ ሆኖ ህጉ እንደገና ተሻሽሏል ተብሏል፡፡

በኮንትሮባንድ እቃዎች ሽያጭ የተገኘው ገንዘብም ገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሰረት እየረቀቀ የመጣውን የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲከላከል ለማስቻል ኮሚሽኑን ለማጠናከር ይውላል ተብሏል፡፡
በሌላም በኩል የተሻሻለው የጉምሩክ አዋጅ የተለያዩ አንቀፆች ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡
ከመካከሉ ኮሚሽኑ በአስመጭዎች እና እቃውን በሸጡላቸው የውጭ ኩባንያዎች መካከል የጥቅም ግንኙነት አለ ፣ የቀረበልኝ የግብይት ዋጋም ትክክለኛ አይደለም ብሎ በጠረጠረ ጊዜ የራሱን የዋጋ የመረጃ ቋት አደራጅቶ በዛ መሰረት ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚችል የተደነገገው ይገኝበታል፡፡
የጉምሩክ ቀረጥ አከፋፈልን በተመለከተ ደግሞ ከዚህ ቀደም የእቃዎች ዋጋ ወደ ኢትዮጵያ ብር ተቀይሮ ቀረጥ የሚከፈለው አስመጭው ዲክላራሲዩን ባስመዘገበበት ጊዜ በነበረው የምንዛሬ ዋጋ ተሰልቶ ነበር፡፡
ይሁንና ዲክላራሲዩን በተመዘገበበት እና በተቀባይነት ባገኘበት ቀን መካከል የምንዛሬ ለውጥ ስለሚኖር መንግስት ከፍተኛ ቀረጥና ታክስ እንዲያጣ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ይላል የአዋጁ ማብራሪያ፡፡
በመሆኑም በማሻሻያው አስመጭው ቀረጥ የሚከፍልበት የምንዛሬ መጠን የሚወሰነው ዲክላራሲዩን ተቀባይነት ባገኘበት ቀን ብሔራዊ ባንክ በገለፀው ጠቋሚ የገንዘብ የምንዛሬ ልክ እንዲሆን በተሻሻለው አዋጅ ተደንግጓል፡፡
በሌላ በኩል እቃዎች በጉምሩክ መጋዘን የሚቆዩበት ቀን ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
አስመጭዎች እቃዎቻቸው የባህርና በየብስ ተጓጉዘው ወደ ሃገር ከገቡ በኋላ በጉምሩክ መጋዘን እንዲያቆዩ የሚፈቅደው 15 ቀን ወደ 45 ቀን ከፍ ብሏል፡፡
በአየር ተጓጉዘው የመጡ ደግሞ በጉምሩክ መጋዘኖች ለ10 ቀን እንዲቆይ ይደነግግ የነበረው አንቀፅ በማሻሻያው ወደ 30 ቀን ከፍ እንዲል መደረጉንም ከአዋጁ ማሻሻያ ተመልክተናል፡፡
በስራ ላይ ያለው የጉምሩክ አዋጅ ኮሚሽኑ እንዲከፍል በጠየቀው ቀረጥ እና ታክስ ያልተስማማ አስጭም ለግብር ይግባኝ ኮሚሽን ይግባኝ እንዲል ይፈቅዳል፡፡
አስመጭው ያንን የሚያደርገው ግን የተጠየቀውን ቀረጥ ታክስ ሙሉ በሙሉከከፈለ በኋላ መሆኑን ይደነግጋል፡፡
ይህም ህገ መንግስቱ ለዜጎች የሰጠውን አቤቱታ የማቅረብ መብት የተጋፋ መሆኑ ተምኖበት አስጪው የተጠየቀውን 50 በመቶ ብቻ አስይዞ ይግባኝ በማቅረብ እንዲከራከር በተሻሻለው የጉምሩክ አዋጅ ተደንግጎ ተመልክተናል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments