የካቲት 3 2017 – የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- Feb 10
- 1 min read
የሱዳንጦር እና የአገሪቱ ወታደራዊ መንግስት መሪ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን አዲስ የጦር ወቅት ባለ አደራ የሽግግር መመስረታችን አይቀርም አሉ፡፡
አልቡርሃን ባላደራውን መንግስት ምስረታ በመዲናዋ ካርቱም የምናካሂደውን የጦር ዘመቻ በፍጥነት ዳር ካደረስነው በኋላ እንመሰርታለን ማለታቸውን ዘ ኒው አረብ ፅፏል፡፡
እንደሚባለው የሱዳን መንግስት ጦር በመዲናዋ ካርቱም በRSF ላይ የበላይነቱን ከማረጋገጡም በተጨማሪ በርካታ ቁልፍ ስፍራዎችን በእጁ አስገብቷል፡፡
አልቡርሃን በሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ከባለሙያዎች የሚውጣጣ ጊዜያዊ ባለ አደራ መንግስት እንደሚመሰረት በፖርት ሱዳን ተናግረዋል፡፡
የሚመሰረተው ባለ አደራ መንግስት ሚኒስትሮች በሚሰየመው ጠቅላይ ሚኒስትር ተመርተው የሚመደቡ ናቸው ብለዋል፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር እና በምህፃሩ RSF የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጦርነት ማካሄድ ከጀመሩ አመት ከ10 ወራት ሊሆናቸው ነው፡፡የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

በሶማሊያ የፑንትላንድ ግዛት ተዋጊዎች በIS ፅንፈኛ ቡድን ታጣቂዎች ተይዞ የቆየን ሰፊ አካባቢን መልሰው ያዙ፡፡
ቀደም ሲል የአሜሪካ የአፍሪካ እዝ (አፍሪኮም) በፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ በፅንፈኞቹ ይዞታ ላይ ከባድ የአየር ድብደባ መፈፀሙን ሬውተርስ አስታውሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፑንትላንድ ግዛት ተዋጊዎች በፅንፈኞቹ ላይ የከፈቱትን ጥቃት አበርትተውታል ተብሏል፡፡
የIS የሶማሊያ ክንፍ የውጭ አገራት ታጣቂዎችም ጭምር ያሉበት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
1 ሺህ 500 ያህል ታጣቂዎች እንዳሉትም ይገመታል፡፡
የሶማሊያ መንግስት ጦር ከሌላኛው ፅንፈኛ ቡድን አልሸባብ ጋር ሲዋጋ ከ17 አመታት በላይ ማስቆጠሩ ይነገራል፡፡
በሊቢያ ደቡባዊ ምስራቅ ክፍል የ28 ስደተኞች የጅምላ ቀብር ተገኘ፡፡
የጀምላ የቀብር ስፍራው የተገኘው ኩፍራ ከተባለው ስፍራ በስተሰሜን እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በዚሁ ስፍራ ከጥቂት ቀናት በፊትም የ17 ሌሎች ስደተኞች የጅምላ የቀብር ሥፍራ መገኘቱ ተጠቅሷል፡፡
በቅርቡ የሊቢያ ሹሞች በህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ኢ-ሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ተይዘው የነበሩ 76 ስደተኞችን እንዳስለቀቁ በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው እወቁልን ብለዋል፡፡
ከዚሁ ወንጀል ጋር በተገናኘ በህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት የተጠረጠሩ አንድ ሊቢያዊ እና 2 የውጭ አገር ዜጎች ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል፡፡
ወደ አውሮፓ ለማምራት ያለሙ ጥገኝነት ፈላጊዎች ሊቢያን በመሸጋገሪያነት እየተጠቀሙባት ነው፡፡
ጥገኝነት ፈላጊዎቹ ባህር ከማቋረጣቸው አስቀድሞ በሊቢያ ብዙ መከራ ስቃይ እና እንግልት እንደሚደርስባቸው ይነገራል፡፡
የእስራኤል ጦር የጋዛ ሰርጥን በሰሜን እና በደቡብ ከሚከፍለው ኮሪደር ለቅቆ ወጣ ተባለ፡፡
የእስራኤልጦር ወታደሮቹን ከኔትዛሪም ኮሪደር ያስወጣው ቀደም ሲል በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በደቡባዊ የሰርጡ ክፍል የቆዩ ፍልስጤማውያን በብዛት ወደ ሰሜናዊው ክፍል እየጎረፉ ነው ተብሏል፡፡
የተኩስ አቁሙ የወደፊት ስጋት ቢጋረጥበትም ፀንቶ እንደዘለቀ ነው ተብሏል፡፡
የታጋቾች እና የእስረኞች ልውውጥም ቀጥሏል፡፡
እስከ ትናንት በስቲያም በሐማስ እጅ የቆዩ 16 ታጋቾች ሲለቀቁ 566 ፍልስጤማውያን እስረኞች ከእስራኤል መፈታታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
የናሚቢያ የነፃነት ትግል መሪ እና የአገሪቱ የመጀመሪያ ፕሬዘዳንት ሳም ኒዮማ በ95 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡
ኒዮማበምህፃሩ ስዋፖ የተሰኘውን የነፃነት ድርጅት በማቋቋም እና ትግሉንም በመምራት አገራቸውን ከዘመኑ የደቡብ አፍሪካ ጥቂት ነጮች አገዛዝ ነፃ በማውጣቱ የተሳካላቸው ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡
ናሚቢያ ከ35 አመታት በፊት ነፃነቷን ካገኘች አንስቶ ለ15 አመታት በፕሬዘዳንትነት መርተዋታል፡፡
ብዙዎቹ ናሚቢያውያን በነፃነት መሪያቸው ሕልፈት ክፉኛ ማዘናቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መንግስታትም የሀዘን መግለጫ መልዕክቶቻቸውን እየላኩ ነው ተብሏል፡፡
የደቡብአፍሪካው ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሣ ሳም ኒዮማን ወደር የለሽ የነፃነት ትግል መሪ ነበሩ ሲሉ አስታውሰዋቸዋል፡፡
የኔነህ ከበደ
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5rs
Comments