የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ለኢትዮጵያ የፅልመት ቀን ነበር፡፡
- 5 hours ago
- 2 min read
ታሪክን የኋሊት
የካቲት 12 / 2018 ዓ.ም
የካቲት 12 ቀን 1929 ለኢትዮጵያ የፅልመት ቀን ነበር፡፡
የስቃይና የመከራ ውርጅብኝ በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ የተቀበሉበት ቀን ነበር፡፡
የካቲት 12 የዋለው አርብ ነበር፡፡ የኢጣሊያው ልዑል ልጅ በመውለዱ ለድሆች ምፅዋት ይሰጣል ተብሎ ተነገረ፡፡
በዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በዚያን ጊዜ ገነት ልዑል ቤተመንግስት፣ ድሆችና ታዋቂ የከተማ ነዋሪዎች ተጠሩ፡፡
ለዝንተዓለም በባዕድ ተገዝታ የማታውቀው ኢትዮጵያ ክብሩዋ ተገሶ፣ ወሰኗ ተደፍሮ፣ በፋሰሽት ኢጣሊያ መወረሩዋ እንደ እግር እሳት የሚያንጋበግባቸው ሁለቱ ወጣቶች አበርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በዚያው ቤተመንግስት ተገኝተዋል፡፡
ሁለቱ ጓደኛሞች ከአጣሊያኖች ጋር የሚሰሩ እንደመሆናቸው በቤተመንግስቱ መገኘታቸው የተለመደ ነው፡፡ ያልተለመደው ያንለት እዚያ የተገኙ ለተለየ ተልኮ መሆኑ ነበር፡፡

ጄኔራል ሮደልፎ ግራዚያኒ በተገኘበት በቤተመንግስቱ በር ፊት ለፊት ለድሆች ምፅዋት መስጠት ተጀመረ፡፡ አይነስውሮች አካል ጉዳተኞች ግቢውን ሞልተውታል፡፡
አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከሚሰጥር ተካፋዩቻቸው ከእነ ሰምኦን አደፍርስ፣ በሻህ ውረድ እና ከበጅሮንድ ለጥይበሉ ጋር ሆነው የወሰኑትን ፣ ጥቃት የማድረስ እቅድ ለመፈፀም ያቺን ቀን መረጠዋል፡፡
ሰዓቱ በግምት ከረፋዱ 4፡00 ሆኗል፡፡
ግራዚያኒና ሌሎች ጄኔራሎች ወዳሉበት አከታትለው የእጅ ቦንብ ወረወሩ፡፡ ቤተመንግስቱ ቀውጢ ሆነ፡፡
ግራዚያኒ ቀላል ጉዳት ገጠመው፡፡ የአየር ሃይል አዣዡ፣ ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ ቄርሎስና ሌሎችም በፅኑ ቆሰሉ፡፡
የኢጣሊያ ሹማምንት ከቦንቡ ፍንዳታ በኋላ ከድንጋጢያቸው ሲነቁ መትረየሳቻቸውን በቤተመንግስቱ ግቢ በነበሩት ኢትዮጵያዊያን ላይ ሁሉ ተከሱባቸው፡፡ ሬሳ በሬሳ ላይ ተነባበረ፡፡
የኢጣሊያ ወታደሮች ማንኛውንም ጥቁር በያለበት እንዲገድሉ ትዕዛዝ ተሰጣቸው፡፡
የፋሽስት ኢጣሊያ ወታደሮች፣ ከቤተመንግስቱ ጀምረው፣ በሁሉም አቅጣጫ ተሰማርተው ኢትዮጵያኖችን ፈጇቸው፡፡
ጥፋተኛ ስለሆኑ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ ተገደሉ፡፡
በአካፋና በዶማ ተቀጠቀጡ ፣ መኪና ተነዳባቸው ፤ ቤታቸው ተቃጠለ፡፡
አገዳደሉ እጅግ አረመኒያዊ ነበር፡፡
በጥይትና በሳንጃ ከሚገድሉት በስተቀር ሕፃናትን ሳይቀር በቤት ውስጥ እየዘጉ አነደዳዋቸው፡፡
መንገዱ በደም ጐርፍ ታጠበ፡፡
ያሰሩዋቸውን በመደዳ ከታሰሩበት እያወጡ በጥይት ጨፈጨፏቸው በመኪና እጅና እግራቸውን እየጉተቱ አስቃዩዋቸው፡፡
ሦስት ቀንም እንደዚህ ሆነ፡፡
ቆስሎም ሆኑ ተገርፎ ነፍሱ የቆየው ለሦስት ቀናት አንድ ጉንጭ ውሃ፣ አንዲት ቁራሽ ጉርሻ አላገኘም፡፡ በረሃብና በጥም አለቀ፡፡
የፋሸሸቶች ልዩ ባህሪው በሆነው ጭካኔ፣ እስከ 30 ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን በሦስት ቀን ተፈፀሙ፡፡ በጊዜው የተማሩና ከጦር ሜዳ የተማሩኩ ወጣቶችን አስቃይተው ገደሏቸው፡፡
አብርሃምና ሞገስ በግርግሩ ውስጥ አምልጠው ወደ አርብኞች ተቀላቀሉ፡፡ በመጨረሻ ወደ ሱዳን ለመሄድ ጠረፍ ላይ ሲደርሱ በኢጣሊያኖች ተይዘው ተገደሉ፡፡
ሰምኦን አደፍርስና በሻህ ውረድንም ጥፍራቸውን እየነቀሉ አስቃይተው ገደሏቸው፡፡
በ1933 ኢትዮጵያ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ የነአብርሃምና በአዲስ አበባ ያለቁት ኢትዮጵያውያን አፅማቸው ተለቅሞ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡
ሞሶሎኒም ግን በገዛ ዜጐቹ ከነሚስቱ ተገድሎ ፣ አስከሬኑ ተዘቅዝቆ ተሰቀለ፡፡
ግራዚያኒም ከማዕረጉ ወርዶ ታሰረ፡፡
እሸቴ አሰፋ












Comments