የካቲት 10 2017 - የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅ መጽደቁ ተነገረ
- sheger1021fm
- Feb 17
- 1 min read
ኢትዮጵያ የሚያጋጥማትን ችግር በራሷ አቅም ለመቋቋም ትችል ዘንድ የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅ መጽደቁ ተነገረ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 42ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በምክር ቤቱ ውይይት ከተደረገባቸው መካከል የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅ የተመለከተው አንዱ ነው፡፡
አዋጁ በተቋሙ የተጀመረውን የሪፎርም ስርዓት ወደ ተግባር በመለወጥ ተረጂነትን በሀገር ውስጥ አቅም መወጣትን ማዕከል በማድረግ የአደጋ ጉዳት ሰለባ ለሆኑ ዜጎች ከሰብአዊ ድጋፍ ከዘላቂ የልማት ፕሮግራሞች ጋር በማስተሳሰር ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ሞራላዊ ጉዳቱን ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል፡፡

ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
ምክር ቤቱ በተጨማሪም በሦስት የተቋማት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ በሥራ ላይ እንዲውሉ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ከዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ ደንብ አንዱ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው አላማውን ለማሳካት የአደረጃጀት ማስተካከያዎችንና የአሠራር ለውጦችን ለማድረግ፤ የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ግሩፕ እና የመከላከያ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ማቋቋሚያ ደንብ ይገኝበታል፡፡
ተቋሙ የሀገሪቱን የልዕለ ሕክምና፣ የዲያግኖስቲክ እና ተዛማጅ አገልግሎት ፍላጎትን ለማሟላት፤ እንዲሁም የተሻለ ህክምና ፍለጋ ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ታካሚዎች በሀገር ውስጥ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማድረግ እንዲሁም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ማቋቋሚያ ደንብ የተቋሙን ተግባርና ኃላፊነት በመደንገግ የሕግ ማዕቀፍ ሆኖ መቅረቡ ተነግሯል።
ምክር ቤቱም በቀረቡት ረቂቅ ደንቦች ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r












Comments