የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ተቀጥረው የሚሰሩት ወጣቶች የኤችአይቪ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ…
- 2 hours ago
- 2 min read
ሰኔ 16/2018
በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ተቀጥረው ከሚሰሩት ውስጥ አብዛኛዎቹ ወጣቶች በመሆናቸው የስነ ተዋልዶ ጤናና የኤች አይ ቪ መከላከልና የህክምና አገልግሎት ላይ በስፋት መሰራት አለበት ተባለ፡፡
10,000 ያህል ሰራተኞች በስሩ የሚያስተዳድረው የአዳማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ በተለይ ሴት ሰራተኞች ለኤች አይ ቪና የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች እንዳይጋለጡ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡
በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ የተቋቋመው የህክምናና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከል በአዳማ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ክትትል እንደሚደረግበትም ተነግሯል፡፡

የወጣቶች ጤና አገልግሎትን በተመለከተ በፓርኩ ውስጥ ባሉ ክሊኒኮች እየሰራን ነው ወጣቶች ሲመጡ ከግንዛቤ ማስጨበጫ ባለፈ ደግሞ የቤተሰብ ምጣኔ፣ ከኤች አይ ቪ እንዴት ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው የማስተማር ስራዎች ይሠራሉ እንዲሁም የምክር እና የምርመራ አገልግሎቶችን ያገኛሉ ሲሉ የአዳማ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሲስተር ሰሚራ መሃመድ ተናግረዋል፡፡
ከልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ሰራተኞች ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች በመሆናቸው በተለይ ከስነ ተዋልዶ ጤና ጋር የተገናኙ አገልግሎቶችን ሙሉ ለሙሉ ስለ ማግኘታቸው ምን ያህል ክትትል ታደርጋላችሁ ያልናቸው ሲስተር ሰሚራ ለክሊኒኩ ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ የሚያስፈልጉ ስታንዳርዶችን ከማሟላት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በቂ የሆኑ ባለሙያዎች አሉ ወይ?
እንዲሁም የስነ ተዋልዶ አገልግሎቶችን፣ ራሳቸውን በራሳቸውን ምርመራ የሚያደርጉበት አገልግሎቶች ከመድሃኒቶች አቅርቦትም ጋር ያሉ ጉዳዮችን እንከታተላለን ብለዋል፡፡
ወጣቶች ይበልጥ ለኤች አይ ቪ እና የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ተጋላጭ በመሆናቸው ቅድመ መከላከሉ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው የሚሉት ደግሞ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ የጤና ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ጋረደው ናቸው፡፡
በስራ ቦታው ላይ ብዙ ወጣቶች አሉ የሚሉት አቶ አለማየሁ ተጋላጭ በመሆናቸውም ኤች አይ ቪ ላይ የኮንዶም አቅርቦትና የግንዛቤ መፍጠር ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የኮንዶም አቅርቦት ላይ ችግር መኖሩ በተደጋጋሚ የሚነገር በመሆኑ በተለይ ኤች አይ ቪን ከመከላከል አኳያ በቂ የኮንዶም አቅርቦት አለ ወይ ስንል የጠየቅናቸው አቶ አለማየሁ የኮንዶም አቅርቦት አሁን ላይ ችግር የለም ነገር ግን አልፎ አልፎ ጤና ጣቢያ ላይ እጥረት ሲኖር ችግሩ እኛም ጋር ይደርሳል ነገር ግን በተቻለ መጠን ኮንዶም በሚሰሩበት ቦታ ላይ ፣ ማደሪያ ክፍሎች እንዲሁም በክሊኒኮች ላይ እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የስነተዋልዶና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ላይ ኤች አይ ቪን ለመከላከል ደግሞ ኮንዶም ከጤና ጣቢያ በፓርኩ ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች ይቀርባል ተብሏል፡፡
በአዳማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ተቀጥረው ከሚሰሩ 10 ሺህ ያህል ሰራተኞች ከ 90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣት ሴቶች መሆናቸው የተነገረ ሲሆን ይህም በተለይ ለኤች አይ ቪ ያላቸውን ተጋላጭነት የሚጨምረው በመሆኑ ቅድመ መከላከሉ ላይ አሁንም የሚጠበቁ ስራዎች አሉ ተብሏል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i





Comments