የእነ አቶ ክርስቲያን ታደለ መዝገብ የዋናው ክስ ብይን ለሐምሌ 3 ተቀጠረ፤
- 9 hours ago
- 1 min read
ሰኔ 16/2018
የእነ አቶ ክርስቲያን ታደለ መዝገብ የዋናው ክስ ብይን ለሐምሌ 3 ተቀጠረ፤ ማረሚያ ቤቱ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት የሚገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና ሌሎች ተከሳሾች ዛሬ ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
ዛሬ ይሰማል ተብሎ ይጠበቅ ለነበረው የዋናው ክስ ብይን ለሐምሌ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ከዚህ ቀደም በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፤ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ሀላፊ ምክትል ኮማንደር ጣሰው ይግዛው በችሎቱ ቀርበው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ተከሳሾቹ ከዚህ ቀደም ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ያቀረቧቸውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ፣ የሕክምና እና ከቤተሰብ ጋር የመገናኘት ችግሮችን በተመለከተ አብዛኞቹ መፈታታቸውን ሀላፊው ለችሎቱ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ተከሳሾቹ ችግሮቹ አሁንም እንዳልተቀረፉ ለችሎቱ አመልክተዋል።
በተለይም ከቤተሰብ ጋር ለመገናኘት መቸገራቸውን፣ በጤና እክል ምክንያት ከቤት የሚመጣላቸው ምግብ ፍተሻው ከመጠን በላይ በመሆኑ እንደሚበላሽ ተናግረዋል።
ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እያገኘ አይደለም ብለዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ፍርድ ቤቱ ፤ የቀረቡት የአያያዝ አቤቱታዎች ከማረሚያ ቤቱ አቅም በላይ እንዳልሆኑ በመጥቀስ ፣ በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸውና የተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ከሦስት ሰዓታት በላይ በፈጀው የዛሬው ችሎት ፤ ፌዴራል ፖሊስ ፣ ተከሳሾቹ አዋሽ አርባ በነበሩበት ወቅት ደረሰብን ስላሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ እንዲያቀርብ የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለማቅረቡ፣ በቀጣይ ምላሽ እንዲሰጥ ታዟል።
ፍርድ ቤቱ በዚህ የአያያዝ አቤቱታ ላይ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ገዛ ጌታሁን





Comments