top of page

የኢትዮጵያ እና የኬንያ የጠረፍ ንግድ መመሪያ

  • 19 hours ago
  • 2 min read

ሰኔ 23/2018


ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑባቸው የድንበር አካባቢዎች የሚገኙ የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ወራዊ የምርት መጠን ግምቱ ከ1000 የአሜሪካን ዶላር የማያልፍ መጠን ያለቸው 50 የምርት ዝርዝሮችን እንዲለዋወጡ የሚፈቅድን መመሪያ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ይፋ አደረገ፡፡


መመሪያው የኢትዮጵያ እና የኬንያ የጠረፍ ንግድ መመሪያ ይሰኛል፡፡


በመመሪያው መሰረት በጠረፍ ንግድ በአንድ ጉዞ ከ2 በላይ የግመል እና ከብቶች ልውውጥ ማድረግ አይቻልም፡፡


መመሪያው የተዘጋጀው በድንበር አካባቢ ህጋዊ የጠረፍ ንግድ ስርዓትን በመዘርጋት በአካባቢው የሚስተዋለውን የኮንትሮባንድ እና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለመቀነስ ስለሚረዳ ነው ተብሏል፡፡


በተጨማሪም በኢትዮጵያ እና በኬንያ ጎረቤት ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በድንበር አካባቢ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን እንደሚረዳ ታምኖበት መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡


በዚህም መሰረት ማንኛውም የጠረፍ ነጋዴ በአንድ ወር ውስጥ የሚያስገባው እና የሚያስወጣው የምርት መጠን ግምት ከ1000 የአሜሪካን ዶላር ወይም ተመጣጣኝ የኢትዮጵያ ብር እና ተመጣጣኝ የኬንያ ሽልንግ መብለጥ የለበትም ይላል መመሪያው፡፡



የሚነግደው ምርት መጠን ከአንድ ሺህ ዶላር እስካልበለጠ ድረስ በወር አራት ጉዞዎችን በማድረግ ምርቶችን ነጋዴዎች መለዋወጥ እንደሚችሉም ተጠቅሷል፡፡


የወጪ ምርቶች የመሸጫ የዋጋ ግምት የሚያሰላው ደግሞ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አልያም እሱ የወከላቸው ተቋማት ናቸው፡፡


ማንኛውም የጠረፍ ነጋዴ የጠረፍ ንግድ ምርቶችን ማስወጣትና ማስገባት የሚችለው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት አገልግሎት በሚሰጥባቸው የድንበር በሮች በኩል ብቻ እንዱሆነም ተደንግጓል፡፡


የደንበር አካባቢ የሚሸፍነው ስፋት ደግሞ በኢትዮጵያ እና ኬንያ የድንበር በር ጀምሮ በኢትዮጵያ በኩል አምሳ ኪሎ ሜትር ሲሆን በኬንያ በኩል መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ያለ ቦታን ያጠቃልላል፡፡


በዚህም መሰረት በአንድ ጉዞ ግመል እና በሬ ከ2 ካልበለጡ እንዲሁም ፍየል እና በግ ደግሞ በአንድ ጉዞ ከ5 ካልበለጡ መገበያየት ይችላሉ፡፡


በቆሎ ደግሞ በአንድ ጉዞ ከአንድ ኩንታል በላይ መገበያት አይቻልም፡፡


እንስሳት ፣የእስሳት ውጤቶች ፣የግብርና ምርቶች፣ቀመማቅመም፣ የምግብ ዘይት ፣ ውሃ ፣ ለስላሳ መጠጦች ፣አልኮል ፣የቆዳ ውጠየቶች ፣አልባሳት ፣ ጫማ፣ የአልሙኒየም ምርቶች፣የስልክ ቀፎዎች ፣ፍራሽ፣የቤትና የቢሮ እቃዎች እንዲሁም የጽፈት መሳሪያዎች በጠረፍ ንግድ እንዲገበያዩ ከተዘረዘሩት ውስጥ ናቸው፡፡


ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ማስወጣት አልያም ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት የሚችለው የተዘረዘሩትን ምርቶች ብቻ ነው፡፡


ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑባቸው የድንበር አካባቢዎች የሚገኙ የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ከመሀል ሀገር በቀላሉ ሊያገኟቸው የማይችሏቸውን መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች በጠረፍ ንግድ እንዲቀርቡላቸው ለማድረግ የሚያስችል የተቀላጠፈ የጠረፍ ንግድ ማዕቀፍ በሁለቱ አገራት መካካል ታህሳስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መፈረሙ ይታወሳል፡፡


መመሪያውም ይህን ለማስፈጸም የወጣ ነው፡፡


ያሬድ እንዳሻው

 
 
 
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page