top of page

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚሰጠው አገልግሎት ደንበኞቹ የእርካታ ደረጃ ከ80 ከመቶ መድረሱን ባካሄድኩት ጥናት አረጋግጫለሁ አለ፡፡

  • sheger1021fm
  • 2 days ago
  • 1 min read

ጥር 19/2018


የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚሰጠው አገልግሎት ደንበኞቹ የእርካታ ደረጃ ከ80 ከመቶ መድረሱን ባካሄድኩት ጥናት አረጋግጫለሁ አለ፡፡


ባንኩ ይህን  ያለው ዘሬ ማካሄድ በጀመረው የደንበኞች አገልግሎት ሳምንት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው፡፡


የኢትዮጵያ ንግድ ባንከ ከዚህ ቀደም በአገልግሎት አሰጣጡ  ላይ በጥቂቱም ቢሆን የታዩ ነበሩ ያላቸውን  ከአሠራር ግልጽነት፣ ከአገልግሎት ጥራት መዋዠቅ፣ ከአገልግሎት መዘግየት፣ ከኔትወርክ መቆራረጥ፣ ከሲስተም ብልሽት፣ ከሥራ ክፍሎች ቅንጅት፡ ከሠራተኞች አመለካከት እና ከሥራ ባህል ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረኩ ነው ብሏል፡፡


የደንበኞች አገልግሎት ሳምንት የሚከበረው በዋናነት ከደንበኞች ጋር በሚካሄዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ግብረ መልስ መሰብሰቢያ ውይይቶች ሲሆን፣ እንደ ደም ልገሳ እና የችግኝ እንክብካቤ የመሳሰሉ ማኅበራዊ ሃላፊነትን መወጫ ተግባራትም ይከናወናሉ ሲሉ የባንኩ ፕሬዚዳንት ተወካይ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ተናግረዋል፡፡


ባንኩ በ2018 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ ከ325 ቢሊዮን ብር በላይተጨማሪ ተቀማጭ በማሰባሰብ፡ አጠቃላይ ተቀማጩን 2 ትሪሊዮን ብር ማድረሱንም አቶ ኤፍሬም ጠቅሰዋል።


የኢትዮጵያ ንግድ ባንከ ቀደም ሲል በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ከሚሰጠው ብድር በተጨማሪ፣በቅርቡ ለባለአነስተኛ ይዞታ እና በቡድን ለተደራጁ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የግብርና ብድር ማመቻቸቱን ሃላፊው አስታውሰዋል፡፡


አነስተኛ የቤት መሥሪያና መግዣ፣ የግል ጉዳይ መፈጸሚያ እና የቤት መኪና መግዣ ብድሮችንም  አስፋፍቻላሁ ሲል ባንኩ ተናግሯል።


የሲቢኢ ብር ፕላስ መተግበርያን ብቻ በመጠቀም ያለምንም ማስያዣ ከ500 እስከ 150 ሺሕ ብር ብድር ማግኘት የሚያስችል ሲቢኢ በጄ" የተሰኘ የብድር አገልግሎት እያቀረበ መቦኑም ተነግሯል።


በቅርቡም ሲቢኢ ኮኔክት የተባለ የዳያስፖራው አባላት ሊጠቀሙበት የሚችሉ የዲጂታል ዋሌት አገልግሎትም  ማስጀመሩ ተጠቅሷል።


ባንኩ ወደፊትም በዚህ መልኩ የደንበኞቹን ፍላጎት ያማከሉ አገልግሎቶችን በተጠናከረ መልኩ ማቅረብ እንደሚቀጥል ኤ ኤፍሬም አረጋግጠዋል፡፡


ንጋቱ ሙሉ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page