''የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ’’ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ወቅት ታይተዋል ያላቸውን ህጸፆች ይፋ አደረገ።
- 2 days ago
- 2 min read
ግንቦት 5/2018
በሰባተኛው ምርጫ ዙሪያ እየሰሩ ካሉ ጥምረቶች አንዱ የሆነው፤ ‘’የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ’’ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ወቅት ታይተዋል ያላቸውን ህጸፆች ይፋ አደረገ።
ማንነትን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን ሳያሟሉ በመራጭነት መመዝገብና በተከለከሉ ቦታዎች የምርጫ ጣቢያዎችን ማቋቋም ጥምረቱ ታይተዋል ካላቸው እንከኖች መካከል ናቸው።
በጥቂት የምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ እና አካባቢ በታጠቁ ኃይሎች በተመዝጋቢዎች፣ በአስፈጻሚዎችና በታዛቢዎች ላይ ጥቃት፣ ማስፈራራትና ወከባ እንተፈጸመም ጠቅሷል።
በምርጫ እና ምርጫ ነክ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰራው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ፤ 2011 ላይ ነው የተመሰረተው።
ከ180 በላይ አባሉት እንዳሉትም ከጥምረቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሃይለማሪያም ሠምተናል።
ከቀናት በኋላ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ሰባተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ዙሪያም የመራጮች ትምህርት በመስጠት እንዲሁም የመራጮች ምዝገባ ሂደትን በመታዘብ ሲንቀሳቀስ እንደቆየ ነግረውናል።

ጥምረቱ ከመጋቢት 12 እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የተከናወነውን የመራጮች ምዝገባ ሂደት ታዝቦ ያሰባሰበውን ግኝትም ይፋ አድርጓል።
ማንነትን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን ሳያሟሉ በመራጭነት መመዝገብ አንዱ እንደሆነ አቶ አበራ ነግረውናል።
በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ ባል ለሚስቱ ፤ እናት ለልጆቿ በመራጭነት ሲመዘገቡ ተስተውሏል ብለዋል።
በህጉ መሰረት ማንኛውም ተመዝጋቢ የቀበሌ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ፤ የመንጃ ፍቃድ ፤ ከውድርና የተገለለለበት ማስረጃ፤
የተማሪ መታወቂያ እና የመሳሰሉ ማስረጃዎችን ለመመዝገብ በማስረጃነት ማቅረብ እንዳለበት ያስታወሱት አቶ አበራ ።
የጥምረቱ ታዛቢዎች ምልከታ ካደረጉባቸው 3 ሺህ 953 የምዝገባ ጣቢያዎች በ494ቱ ግን እነዚህ ማስረጃዎች ሳይሟሉ ሰዎች በመራጭነት ሲመዘገቡ ታይቷል ብለዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የምርጫ ጣቢያዎች በተከለከሉ ቦታዎች ተቋቁመው የጥምረቱ ታዛቢዎች መመልከታቸውን ነግረውናል።
ህብረቱ ከታዘባቸው 3870 የምዝገባ ጣቢያዎች በ424ቱ ያልተፈቀደላቸው የቀበሌ አመራሮች እና አስተዳደሮች ፤ የፀጥታ አካላት እና የአካባቢ የፓርቲ አስተባባሪዎች ተገኝተው ተመልክተናል ብለዋል።
የምርጫ ህጉ በምዝገባ ጣቢያዎች ተመዝጋቢዎች ተመዝግበው እስኪጨርሱ፣ ከምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎችና ሠራተኞች፣ ከፓርቲ ወኪሎች እንዲሁም ዕውቅና ካላቸው ታዛቢዎች ውጭ ማንኛውም ሌላ አካል መገኘት የለበትም በሚል እንደሚከለክል አቶ አበራ አስታውሰዋል።
በጥቂት የምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ እና አካባቢ የታጠቁ ኃይሎች በተመዝጋቢዎች፣ አስፈጻሚዎች፣ታዛቢዎች ላይ ጥቃት፣ ማስፈራራት፣ ወከባ ሲፈጸሙ ታዛቢዎቹ መመልከታቸውን ጨምረው ነግረውናል።
ለአካል ጉዳተኞች እና ልዩ የመንቀሳቀስ ውስንነት ላለባቸው ሰዎች ምቹ ያልሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ብዙ እንደሆኑ የጥምረቱ ታዛቢዎች መመልከታቸውም ተጠቅሷል።
ከመጋቢት 12 እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የተከናወነውን የመራጮች ምዝገባ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ፤ የጎላ ችግር ያልታየበት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሃይለማሪያም ነግረውናል
ኅብረት ለምርጫ፤ የመራጮች ምዝገባ ሂደትን ታዝቦ ግኝቶቹን ይፋ ያደረገው ከትግራይ ክልል እና አከራካሪ ከሆኑ ቦታዎች በስተቀር፤
በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ካሰማራቸው 522 ታዛቢዎቹ ካሰባሰበው መረጃ እንደሆነ ሠምተናል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ…..
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments