የኢትዮጵያ ሂሳብ አዋቂዎች እና ኦዲተሮች ማህበር ከፍተኛ ቅሬታ የቀረበባቸውን የቦርድ አባላት በአዲስ ተካ፡፡
- sheger1021fm
- 15 hours ago
- 3 min read
ጥር 12/2018
የኢትዮጵያ ሂሳብ አዋቂዎች እና ኦዲተሮች ማህበር "ስራቸውን በአግባቡ አልሰሩም፣ ህግን አላከበሩም ፣ ኦዲት ሪፖርት ለዓመታት አላቀረቡም ፣ጠቅላላ ጉባዔም ወቅቱን ጠብቀው ማካሄድ አልቻሉም"በሚል ከፍተኛ ቅሬታ የቀረበባቸውን የቦርድ አባላት በአዲስ ተካ፡፡
የቀድሞ ቦርድ አባላት ስራቸወን በአግባቡ ባለመስራታቸው እና ሪፖርት ባለማቅረባቸው "ይቅርታ" ጠይቀዋል፡፡
ከ600 በላይ ንቁ በስራ ላይ ያሉ ድርጅቶች አባላት ያሉት ማህበሩ ጥቅላላ ጉባዔውን እና የምስረታ 50ኛ ዓመቱን ጥር 9 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ፋካሊቲ የመሰብሰብያ አዳራሽ አካሂዷል፡፡
የተከናወኑ ስራዎችን እና ዓመታዊ ሪፖርት እንዲቀርብ ወደ መድረክ ወጥተው የነበሩት የማህበሩ ፕሬዚዳንት እና የቦርድ አባላት በአግባቡ የተቀናጀ ሪፖርት አሰናድተው ማቅረብ ተስኗቸው ታይቷል፡፡
ይህን ተከትሎ ሃሳብ የሰጡት ለ41 ዓመታት ያክል የማህበሩ አባል ሆነው መቆየታቸውን የተናገሩት አቶ ታዬ ከበደ የተባሉ ተሳታፊ ሙያው የተከበረ መሆኑን አስታውሰው "ግን እኛ አዋርደነዋል ፣ሰርቀንዋል"ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ማንም ሰው ከመተዳደርያ ደንቡ ማለፍ እንደሌለበት ቢደነግግም ማንም ደንቡን እያከበረ አይደለም ካሉ በኋላ ለማሳያ ደንቡ የዓመቱ መጨረሻ ሰኔ 30 እንደሆነ እና ከ90 ቀን በፊት ስብሰባ ይጠራል ነው የሚለው ፤ ከመስከረም 25 በኋላ ቦርዱ ስብሰባ የመጥራት መብት የለውም ብለዋል፡፡
አቶ ታዬ በማከልም ማህበሩ እራሱን በራሱ የገደለ ተቋም ነው ያሉ ሲሆን አሁን ቦርዱ የሃላፊነት ጊዜ ስላበቃ ይህን የማድረግ ሃላፊነት የላችሁም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሂሳብ አዋቂዎች እና ኦዲተሮች ማህበር አባላቱን ጠቅላላ ጉባዔ አይጠራም ፣ሲጠራም ግልጽ አይደለም፤ በስልክ መልክዕት አይልክም በጋዜጣም ማስታወቂያ አያስነግርም ሲሉ አቶ ታዬ አክለዋል፡፡
የቀድሞው ማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዮሃነስ ንጋቱ አቶ ታዬ ያነሱትን ሃሳብ እና ትችት እንዲጨርሱ አልፈቀዱላቸውም፡፡ አቶ ዮናስ እኛ ልንወቀስም ፣ልንከሰስም አይገባም መክንያቱም የተሰጠኝ እቅደም የለም የምንሰራው በፍቃደኝነት ነው እንጂ ተከፍሎን አይደለም የምንሰራው ሲሉ ተናገረዋል፡፡
የተፈጠረውን ስህተት በእኛ ብቻ ሳይሆን በጋራ ድክመታችን የተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔውንም በወቅቱ ሳናካሄድ የቀረነው በተደጋጋሚ ጠርተን ጉባዔውን ለማካሄድ የሚያስችል አባላት መጥተው መገኘት ባለመቻሉ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
አቶ ዮሃንስ አንዳንድ ትችቶች ግለሰብ ላይ ያነጣጠሩ ናቸውም ብለዋል፡፡
ሌላ አንድ ስሙን ለመናገር ያልፈቀደ የውይይቱ ተሳታፊ እና የማህበሩ አባል ቦርዱ ባለፉት አራት አመታት በአግባቡ ሪፖርት አቅርቦም ሆነ እቅድ አውጥቶ እንደማያውቅ ነግረውናል፡፡
አባሉ በተጨማሪም በማህበሩ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ቡድናዊነት እንዳለ እና የሚሰራውም በትውውቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ፕሬዚዳንት ተደርገው የሃላፊነት ቦታውን የተረከቡት አቶ ብርሃኑ ሸፍኔ በበኩላቸው ለዚህ ችግር ተቋሙን የዳረገው የቦርድ አባላት የነጻ አገልጎለት ወይንም በበጎ ፍቃድ የሚሰራ መሆኑ አንዱ ችግር እንደሆነ አስረድተዋል ፡፡
ስራ ሲኖር ሁሌም ስህተት ይኖራል ያሉት አቶ ብርሃኑ ችግር የሚሆነው ስህተትን በስትት ለማረም ሲሞከር ነው ስህተትን ማረም ተገቢ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ስህተቶች ብቻ ሳይሆን ጥንካሬዎችም መኖራቸውን ተናግረው ይህ ማለት ግን የሆነው ሁሉ ልክ ነው ማለት አይደለም ፤ለዚህም ስህተቶች መታረም አለባቸው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሌላው የቦርድ አባል አቶ ኡመር በበኩላቸው ማህበሩ በርካታ ስራዎችን መስራቱን ጠቅሰው ስራዎችን አቀናጅተን ማቅረብ ባለመቻላችን ይቅርታ እንጠይቃለን ሲሉ ተማጽነዋል፡፡
የሚጠበቅብንን አልሰራንም ያሉት አቶ አሙር የተሰራውም ቢሆን በአግባባ ማቅረብ ባለመቻሉ አዝናለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እየተገናኘን እየተነጋጋርን አልነበረም በዚህ ተረዱን ሲሉ አቶ ኡመር አስረድተዋል፡፡
ሌላው የቦርድ አባል አቶ ይርጉ ታምሬ ማህበሩ የእድሜውን ያክል እንዳልሰራ ጠቅሰው ነገር ግን ይህን አቅዳችሁ ይህን ስሩ ያለን አካል የለም፤ የማህበሩ አባላትም ፍላጎት በጣም ሰፊ ነው በለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ሙያው በራሱ ፈተና ውስጥ ነበር ያሳለፈው የሚሉት የቦርድ አባሉ፣ በዚህም ምክንያት ወቅቱን ጠብቆ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ አላስቻለንም ብለዋል፡፡
ከዚያ በተጨማሪም የማህበሩ አባላት ሁለቴ ጠርተን ሳይመጡልን ቀርተዋል፡፡ አሁንም ጉባዔ ያካሄድነው የምስክር ወረቀት እንሰጣለን ብልን ጠርተን ነው ሲሉ አቶ ይርጉ ተምሬ አስረድተዋል፡፡
ጥር 9 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ሂሳብ አዋቂዎች እና ኦዲተሮች ማህበር አዲስ ሰባት የቦርድ አባላትን በመምረጥ እና የአባላትን መዋጮ ዓመታዊ ክፍያ ከ1500 ብር ወደ 5,000 ብር በማሳደግ አጠናቋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…..
YouTube : https://url-shortener.me/2DTR
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://url-shortener.me/2DTY
WhatsApp :https://url-shortener.me/2DU0
X : https://x.com/shegerfm?s=2
Website፡ https://www.shegerfm.com/
LinkedIn :https://url-shortener.me/2DU8
Tiktok : https://url-shortener.me/2DUB
Instagram : https://url-shortener.me/2DUD












Comments