top of page

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መክፈል የሚጠበቅባቸው የቅጣት ገንዘብ ላይ ምሕረት ማድረጉን ተናገረ።

  • 31 minutes ago
  • 1 min read

መጋቢት 8/2018


የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መክፈል የሚጠበቅባቸው የቅጣት ገንዘብ ላይ ምሕረት ማድረጉን ተናገረ።


ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በተለያየ ምክንያት የቆዩ ሰዎች ከቪዛ ጊዜ በላይ ለቆዩበት በየቀኑ በዶላር የሚሰላ ቅጣት ይጣልባቸዋል።


የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንዳለው ለገንዘብ መቀጮ የተዳረጉ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ገንዘቡን የመክፈል አቅም እንደሌላቸው ጠቅሰው ቅጣቱ  እንዲነሳላቸው ጥያቄ አቅርበዋል ብሏል።


በጥያቄው መሰረት ጉዳዩን ተመልክቼዋለው ያለው ተቋሙ ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ቅጣቱ ሙሉ ለሙሉ ተነስቶላቸዋል፤ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ደግሞ ከቅጣቱ ግማሹን እንዲከፍሉ ወስኛለሁ ብሏል።


ይህ በትውልድ ኢትዮጵያዊ፣በዜግነት አሜሪካዊ ለሆኑ ዜጎች የተደረገው ምሕረት ወደ ህጋዊ የቪዛ ስርዓት እንዲገቡ በሚል የተወሰነ መሆኑ ተነግሯል።



ከመጋቢት 15 እስከ ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ በመጠቀም ወደ ህጋዊ ስርዓቱ እንዲገቡም ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።


ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለተለያየ ጉዳይ የመጡ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራዎች ከቪዛ ጊዜያቸው በላይ ሲቆዩ በየቀኑ በዶላር የሚከፈል ቅጣት የሚጠብቃቸው ሲሆን አንዳንዶቹ ያለባቸው ቅጣት በብዙ ሺህ ዶላሮች መሆኑን ሲናገሩ ይሰማል።


በተለይ ሙሉ ቤተሰብ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ የመጡና የቪዛ ጊዜያቸውን ያሳለፉት ላይ ቅጣቱ ከፍተኛ ሆኖባቸዋል።


ይህንን ከፍተኛ የቅጣት ገንዘብም ለመክፈል መቸገራቸውን በመጥቀስ ምሕረት እንዲደረግላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል ብሏል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት።


ኢትዮጵያ የሌላ ሀገር ዜግነትን የሚወስዱ ተወላጆቿ የኢትዮጵያ ፓስፖርታቸውን ይዘው እንዲቆዩ የሚያደርገውን ጣምራ ዜግነትን አትፈቅድም።


የጣምራ ዜግነትን ብትፈቅድ በዓለም ዙሪያ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በቀላሉ ወደ ሀገራቸው መግባትና መውጣት ይችላሉ የሚለው አስተያየትም የረጅም ጊዜ ጥያቄ መሆኑ ይታወቃል።


ቴዎድሮስ ወርቁ

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page