top of page

በዚህ ዓመት ዝርያቸው ከተዳቀሉ 4.4 ሚሊዮን ከብቶች ውስጥ 2.4 ሚሊዮን የተዳቀሉ ከብቶች ሳይሳካ ቀርቷል ተብሏል።

  • 3 days ago
  • 1 min read

ሐምሌ 2/2018


በዚህ ዓመት ዝርያቸው ከተዳቀሉ 4.4 ሚሊዮን ከብቶች ውስጥ 2.4 ሚሊዮን የተዳቀሉ ከብቶች ሳይሳካ ቀርቷል ተብሏል።


ከተዳቀሉት ውስጥ የተወለዱት ጥጃዎች 2 ሚሊዮን ብቻ ነው ተብሏል፡፡


ይህ የተባለው የግብርና ሚኒስቴር ላለፉት 4 ዓመታት እየተተገበረ ያለውን የሌማት ትሩፋትና የበጀት ዓመቱን የእንስሳትና የዓሣ ምርትን በተመለከተ በተሰጠው መግለጫ ነው።


የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)ባለፉት አመታት 228 የመኖ ማቀነባበርያዎች ወደ ስራ መግባታቸው የጠቀሱ ሲሆን ነገር ግን አሁንም ድረስ የእንስሳት መኖች ችግር አልተቀረፈም ብለዋል።


የተሰሩት ማቀነባበርያዎች እና የሚመረተው የመኖ ምርት ከእንስሳቱ ቁጥር ጋር ግን የተመጣጠነ እና በቂ አይደለም ተብሏል።


በበጀት ዓመቱ 420 ሺህ ቶን ማር ፣ 250 ሺህ ቶን የዶሮ ስጋ ፣ 11 ቢሊዮን እንቁላልና 15 ቢሊዮን ሊትር ወተት መመረቱን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሣ ተናግረዋል።


በሌማት ትሩፋት ስራ በዶሮ ስጋና እንቁላል ፣ በወተት ምርት በማርና በዓሣ ምርት ጭማሪ መታየቱን ጠቅሰዋል።


በወተት እና በዶሮ ምርት ላይ የሀገር ውስጥ እንስሳት ምርት እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ፍቅሩ የተዳቀሉና ዝርያቸው የተሻሻሉ እንስሳት ግን ከሀገር በቀሉ የበለጠ ምርት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።


ለዚህ ስራ ትልቁ ችግር የመኖ አቅርቦት መሆኑ የተነገረ ሲሆን በተለይም የተቀነባበረ መኖ እጥረት መኖሩንም አንስተዋል።


በአሁኑ ሰዓት 228 የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያዎች መኖራቸው በግብርና ሚኒስቴር ተመዝግቧል የተባለ ሲሆን በዚህ ዓመት 15 የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች ተገዝተው ለክልሎች መሰራጨቱን ሚኒስትር ዲኤታው አብራርተዋል።


መንግስት የእንስሳት መኖ እጥረትን ለመፍታት አሁንም የተለያዩ አማራጮችን እየፈለገ ነው ያሉት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ፍቅሩ አሁንም የመኖ ማቀነባበርያ ማሽኖች ተገዝተው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።


የዶሮ ምርትን ለማሳደግ የጫጩት ማስፈልፈያ በ4 ስፍራዎች መቋቋሙን ያስረዱ ሲሆን በአመት እስከ 60 ሚሊዮን ጫጩት ማስፈልፈል የሚያስችል ፋብሪካ እየተገነባ ነው ተብሏል።



በረከት አካሉ

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page