top of page

የባህርማዶ ወሬዎች - ሐምሌ 8 2017

  • sheger1021fm
  • Jul 15
  • 1 min read
ree

ዩክሬይን

የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት የአገሪቱን የጦር ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ማራዘሚያ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማው ይሁንታ አቀረቡ፡፡

ለፓርላማው የቀረቡት የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቆች ሁለት መሆናቸው አናዶሉ ፅፏል፡፡

አንደኛው ራሱን የአስቸኳይ ጊዜው የተመለከተ ነው ተብሏል፡፡

ሌላኛው ደግሞ የሰራዊት አባላትን ምልመላ እና ክተትን የተመለከተ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ሕጎቹ በፓርላማው ከፀደቁ በኋላ በፕሬዘዳንቱ ተፈራርሞባቸው ከወር ባነሰ ጊዜ ስራ ላይ መዋል እንደሚጀምሩ ታውቋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜው ከጦርነቱ አንስቶ እየተራዘመ ስራ ላይ ቆይቷል ተብሏል፡፡

ዩክሬይን ከ3 አመታት በላይ ከሩሲያ ጋር በጦርነት ላይ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡

ree

ሶማሊያ

የሶማሊያው ፅንፈኛ ቡድን አልሸባብ ታርዶ ከተማን ከመንግስት ጦር ደጋፊ ታጣቂዎች መንጠቁ ተሰማ፡፡

ታርዶ በሶማሊያ ማዕከላዊ ክፍል ሒራን ግዛት የሚገኝ ከተማ ነው፡፡

የመንግስት ጦር እና ተባባሪዎቹ ታርዶን ለማስመለስ መልሶ ማጥቃት መክፈታቸውን ሬውተርስ ፅፏል፡፡

ፅንፈኞቹም ጥቃታቸውን ወደ አቅራቢያው አካባቢዎችም የማስፋት እቅድ አላቸው ተብሏል፡፡

አልሸባብ ላለፉት ሰባት ወራት በታርዶ አካባቢ ጥቃቱን ሲያፋፍም መቆየቱ ይነገራል፡፡

በአፍሪካ ህብረት ሀይል የሚታገዘው የሶማሊያ መንግስት ጦር ከፅንፈኛው ቡድን ጋር ሲዋጋ ከ16 አመታት በላይ ሆኖታል፡፡

ree

 

ጀርመን

የጀርመኑ መራሄ መንግስት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር የጋዛ ፍልስጤማውያንን ሰብስቦ በራፋ መጠለያ ሰፈር የማጎር ውጥን በብርቱ ነቀፉት ተባለ፡፡

የእስራኤል መንግስት የራፋውን የፍልስጤማውያን ማሰባሰቢያ መንደር ግንባታውን እወቁልኝ ማለት ከጀመረ መሰንበቱን ሚድል ኢስት ሞኒተር አስታውሷል፡፡

የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ጦሩ ጉዳዩን በተመለከተ ዝርዝር እቅድ እንዲያቀርብ ያዘዙት ቀደም ብሎ ነው፡፡

የጀርመኑ መራሄ መንግስት ፍሬድሪክ ሜርዝ የእስራኤል መንግስት የራፋ እቅድ በጭራሽ ተቀባይነት የለውም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

በእስራኤል መንግስት ውጥን መሰረት ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የጋዛ ሰርጥ ፍልስጤማውያን የግዴታ በራፋ መጠለያ እንዲሰበሰቡ ይደረጋል፡፡

እስራኤል በአሁኑ ወቅት በጋዛ የጦር ዘመቻ ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡

ree

እንግሊዝ

በእንግሊዝ አንዲት መለስተኛ አውሮፕላን በመከስከሷ የ4 ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡

አውሮፕላኗ ወደ ኔዘርላንድስ ለማምራት ከሳውዝ ኢንድ ኤርፖርት እንደተነሳች መከስከሷን AFP ፅፏል፡፡

በአደጋው የሞቱት የውጭ አገራት ዜጎች ናቸው ተብሏል፡፡

የየትኞቹ አገሮች ዜጎች እንደሆኑ ግን በዝርዝር አልተጠቀሰም፡፡

አደጋው የደረሰበት የሳውዝ ኢንድ ኤርፖርት ከርዕሰ ከተማዋ ለንደን በ65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው ተብሏል፡፡

በእንግሊዟ ርዕሰ ከተማ ለንደን አካባቢ 6ኛው ታላቅ ኤርፖርት ነው ተብሏል፡፡

አውሮፕላኗ በምን ምክንያት ልትከሰከስ እንደቻለች ለጊዜው የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡

ተለዋጭ መመሪያ እስኪሰጥ ኤርፖርቱ ተዘግቶ እንደሚቆይ ተጠቅሷል፡፡

የኔነህ ከበደ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page