top of page

“የሰኔ እዳው ሰኔና ሰኞ የገጠመ እለት ነው”

  • Jun 8
  • 2 min read

“የሰኔ እዳው ሰኔና ሰኞ የገጠመ እለት ነው”


"ሰኔና ሰኞ" በኢትዮጵያ ባህላዊ ግጥሞች ውስጥ ፍጹም የማይገናኙ ወይም ሲገናኙ አደጋ የሚያመጡ ነገሮችን ለመግለጽ እንደ ዘይቤ ሲያገለግል ይስተዋላል። ይኽ ግጥምጥሞሽም በየተወሰነ ዓመታት (በ5፣ በ6 እና በ11 ዓመታት ልዩነት) በአንድ እለት የሚገጥም ሲሆን፣በብዙዎች ዘንድም እንደ መጥፎ እድል ተደርጎ ሲወሰድ ይስተዋላል።


⁉️ለመሆኑ የሰኔና ሰኞን መግጠም እንደ መጥፎ እድል (ሚልኪ) የማየት ልማድ ከየት ተጀመረ?


በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የሸዋ ገዢ የነበሩ በመርዕድ አዝማች ወሰን ሰገድ መንዝና ይፋት (ተጉለት) ውስጥ በሚኖሩበት ወቅት ቤዛነ ወልድ የሚባል ተማሪን የማይስማማኝ ወር ንገረኝ ቢሉት ሰኔና ሰኞ የገጠመ እለት ለእርሶ አይስማማዎትም እንዳላቸው እና ከ4 አመት በኋላ ሰኔና ሰኞ በገጠመ እለት ንጉሡ በማረፋቸው (በመገደላቸው)፣ በሕዝቡ ዘንድ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቀኑ እንደ መጥፎ እድል እየታየ መምጣቱን በጨዋታ እንግዳ ዝግጅት ላይ እንግዳ ሆነው ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ ተናግረዋል።



ሌላው ሕዝቡ ይህንን ቀን እንደ መጥፎ ዕድል እንዲያይ ያደረገው በ1950ዎቹ መገባደጃ አካባቢ የወጣው የትራፊክ አዋጅ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል።


ለአሽከርካሪዎች የመኪና መሪ በስተቀኝ በኩል እንዲሆን አዋጁ ሲወጣ ከዚያ ቀደም እንደ አሁኑ የመኪና መሪ በስተግራ በኩል ነበር፤ አዋጁ ተፈጻሚ መሆን የጀመረበት ዕለት ሰኔና ሰኞ የገጠሙበት ቀን ነበርና ልማዱን ያልቀየረውና ሁልጊዜ ወደ ግራ እያየ የሚሻገረው እግረኛ፣ በድንገት መኪና ከቀኝ በኩል እየመጣ አደጋ ይደርስበት ስለነበር የብዙ ሰው ሕይወት ጠፍቷል። በዚህም ሕዝቡ ግጥምጥሞሹን እንደ መጥፎ እድል ከክፉ ነገር ጋር አያይዞታል የሚሉት ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ ናቸው።


የሰኔና ሰኞ ፍርሃት በደንብ የተጠና ሳይንሳዊ ወይም ሃይማኖታዊ መሠረት ያልተገኘለት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ በታሪካዊ አጋጣሚዎች የተፈጠረ ፎክሎር ነው የሚሉ አሉ።


ታዋቂው የቃላት መዝገብ ጸሐፊ ደስታ ተክለወልድም በመጽሐፋቸው"የመለኛ የጠንቋይ ፈሊጥ ሰኔና ሰኞ በባተ ቁጥር ማስፈራሪያ ሆነው ይኖራሉ" በማለት ነገሩ የአስተሳሰብ እንጂ የቀኑ ክፋት እንዳልሆነ ይገልጻሉ።


ነገር ግን በግጥምጥሞሹ ማመን ወይም አለማመን የግል ምርጫ ቢሆንም ሁልጊዜም አገር ከፈተና እንድትድን በየእምነቱ መጸለይና በጥንቃቄ መጓዝ ይገባል።


እንሆ ዘንድሮም ዘመን ቆጥሮ ሰኔና ሰኞ ተገጣጥሟል። መልካም የወሩም የሳምንቱም መጀመሪያ ቀን ይሁንላችሁ።


ትዕግሥት ፍሥሐ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page