የሜትር ታክሲ አገልግሎት አቅራቢው ''ያንጎ'' ከአዲስ አበባ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀዋሳ ከተማ ሥራ በመጀመሩ ተሰማ።
- 9 hours ago
- 1 min read
ሰኔ 1/2018
የሜትር ታክሲ አገልግሎት አቅራቢው ''ያንጎ'' ከአዲስ አበባ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀዋሳ ከተማ ሥራ በመጀመሩ ተሰማ።
በሀዋሳ ባጃጅ፣ ባለ4 እግር ባጃጅ እና የሞተር ሳይክል አገልግሎቶች አሁን በያንጎ መተግበሪያ ላይ አሉ የተባለ ሲሆን፤ ተሳፋሪዎች በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጉዞዎቻቸው 30 በመቶ በመቶ ቅናሽ ያገኛሉ ተብሏል።
ያንጎ ሀዋሳ ከኤልና ትሬዲንግ እና ኮንትራስት ትሬዲንግ ጋር በመተባበር መቅረቡን ኩባንያው ከላከልን መግለጫ ላይ ተመልክናል።
ያንጎ በሀዋሳ ሁለት አይነት ተሽከርካሪዎችን በሁለት የታሪፍ ክፍሎች ሥራውን ጀምሯል ተብሏል።
አንደኛው“ባጃጅ ታሪፍ” የተባለ ሲሆን ይህም ሁለት ልዩ ባለ ሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎችን ማለትም ባለ 3 እና 4 እግር ባጃጆችን ያካትታል ተብሏል።
ሁለተኛው አማራጭ “ሞቶ ታሪፍ” የሚባል ሲሆን ይህ ደግሞ የሞተር ሳይክል ጉዞ አገልግሎት ይሰጣል ሲል ያንጎ አስረድቷል።

ያንጎ ከአዲስ አበባ ውጪ የጉዞ ማዘዣ አገልግሎቱን ያስፋፋበት የመጀመሪያ ከተማ አዋሳ መሆኗንም ኩባንያው ጠቅሷል።
“ሐዋሳ በኢትዮጵያ በጣም ንቁና በፍጥነት እያደጉ ካሉ ከተሞች አንዷ ስትሆን፣ ለዲጂታል አማራጮች ዝግጁ የሆነ የትራንስፖርት ሥርዓት አላት” ያሉት የያንጎ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ይቀናዓለም አበበ (ዶ/ር) “ዓላማችን ለተሳፋሪዎች እያንዳንዱን ጉዞ የበለጠ ምቹ ማድረግ ሲሆን፣ ይህን አገልግሎት ለሚያንቀሳቅሱ አጋር አሽከርካሪዎችም የበለጠ ጥቅም የሚያስገኝ እንዲሆን ማድረግ ነው” ብለዋል፡፡
በሀዋሳ የሜትር ታክሲ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ያንጎ መሰረቱን ከሩሲያ አድርጎ ዋና መቀመጫውን በዱባይ ያደረገ ኩባንያ ሲሆን በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከህዳር ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡
የያንጎ ግሩፕ፣ የትራንስፖርት፣ የማድረስ፣ የፉድቴክ፣ የመዝናኛ እና ሌሎች ዲጂታል አገልግሎቶቹን በአፍሪካ ውስጥ ባሉ ከ30 በላይ ሀገራት፣ በላቲን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በደቡብ እስያ እና ሌሎች የዓለም ሀገራት ውስጥ ይሰጣል።




Comments