የሚመጣው የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሁሉ ጠቃሚ ነው ወይ?
- 1 hour ago
- 2 min read
ግንቦት 29/2018
መንግስት በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያ የውጪ ኢንቨስትመንት እያደገ እንደመጣ ሲናገር ይደመጣል፡፡
በበጀት ዓመቱ 9 ወራት ብቻ ከውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ 3.52 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ ተነግሯል፡፡
የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማደግ በተለይ ለአዳጊ ሀገሮች የበረከቱ ጥቅሞች እንዳሉት የሚነገር ሲሆን ዘርፉ ግን ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄም እንደሚሻም የዘርፉ ባለሞያዎች ያስረዳሉ፡፡
በተለይ አንድ የውጪ ኢንቨስተር ወደ ሀገር ቤት ለማልማት ብሎ ሲመጣ ከፍቃድ አስጣጥ ጀምሮ በጠቅላላ በልማት ሒደቱ የጠበቀ ቁጥጥር እና ክትትል ሊደረግበት ይገባልም ይላሉ፡፡
ይህ ካልሆነ ግን በኢንቨስትንት ስም ፈቃድ ወስደው የሀገሪቱ ህግ ከሚፈቅደው ውጪ ሀገሪቱን በሚጎዱ ተግባራት የመሰማራት እድል እንዳላቸው የሚያስጠነቅቁም ብዙዎች ናቸው፡፡

እነዚህ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስራን ፍቃድ የሚሰጠው እና የሚፈቅደው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም የሀገሪቱን ህግ አክብረው የሚሰሩ ውጤት እያመጡ ያሉ የውጪ ኢንቨስተሮች እንዳሉ ሁሉ ህግ ጥሰው ሲሰሩ የማገኛቸው ፍቃድ የወሰዱ ኢንቨስተሮች እንደሚያጋጥሙም ጠቅሷል፡፡
ለመሆኑ በውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ አካላት ወደ ሀገር ገብተው ጉዳት እንዳያደርሱ ምን አይነት ጥንቃቄዎች ሊደረጉ ይገባል? ሁሉም አይነት ከውጪ የሚገቡ አልሚዎች ለሀገር ጠቃሚ ናቸው ማለትስ ይቻላል ወይ? ስለጉዳዩ የዘርፉን ባለሞያዎችን ጠይቀናል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚኪስ አሶሴሽን ከፍተኛ አማካሪ እንዲሁም የደሎፕመንትና ዌልፌር ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር ሞላ አለማየሁ በዘርፉ ፈቃድ ሲሰጥ ለሀገር ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን በትኩረት መፈተሸ እንደሚገባው የሚያስረዱ ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ሊያመዝን የሚችልበት ዕድል ሊፈጠር እንደሚችልም ይጠቅሳሉ፡፡
በሀገር ውስጥ እና በአለም ድርጅቶች ወስጥ በፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ አማካሪ የሆኑት ጥላሁን ግርማ በበኩላቸው አንድ የውጪ ኢንቨስተር ገንዘብ ይዞ ስለመጣ ብቻ መቀበል ሳይሆን የሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት ይኖር እንደሆነ መመርመር እንደሚስፈልግም ያብራራሉ፡፡

ያ ካልሆነ ግን ኢንቨስተሮቹ የተለያዩ ጎጂ ፍሳሾችን በመልቀቅ ከፍተኛ ብክለት በማስከተል ህብረተሰቡን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከተሉ የሚችሉ፣ ግብርን በአግባቡ የማይከፍሉ እና መሰል ችግር ያለባቸው እንደሚኖሩም ያስረዳሉ፡፡
በገቡበት ቃል መሰረት የማይሰሩ እነዚህ የውጪ ኢንቨስተሮች በተለይ ድሀ ሀገራት ላይ አላማቸው ለማሳካት እንደሚቀላቸው ስለሚያምኑ በርትተው እንደሚሰሩም ዶ/ር ሞላ አለማየሁ ያስረዳሉ፡፡
ከአፍሪካ ሀገራት በእነዚህ አይነት ኢንቨስተሮች ጉዳት እየደረሰባት ነው ያሏትን ኮንጎን እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ በዘርፉ ሙስና መሰል አሰራሮችን እንደ መግቢያ በር ሊጠቀሙባቸው ስለሚችል እዚህም ላይ ብርቱ ቁጥጥር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እኚህን ሀገርን ይጎዳሉ የሚባሉት ኢንቨስተሮች በሀገር ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ታዲያ ምን መደረግ ይኖርበታል ያልናቸው የፋይናንስ እና ኢንቨስተምንት አማካሪው አቶ ጥላሁን ግርማ፤ የኢንቨስትመንት አዋጭነት ጥናት እና ተያያዥ የኢንቨስተሩን የቀደሙ ታሪኮች በደንብ መፈተሽ ይገባል ሲሉ መልሰዋል፡፡
በተጨማሪም ለኢንስተሮቹ ፍቃድ ሲሰጥ ግልጽ የሆነ የጊዜ ገደብ እንደሚያስፈልግ፣ በተቻለ መጠን የሀገሪቱን የኢንቨስትምንት ፖሊስ በአግባቡ እንዲረዱት ማድረግ እና በዘርፉ የተቀመጡ መመሪያዎች እና ህጎች ግልፅ ማድረግ እንደሚየስፈልግም ባለሞያዎቹ መከረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ከሰሞኑ 9 ወራት የስራ አፈጻፀሙን በፓርላማ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ባስረዱበት ወቅት፤ ባለፉት 9 ወራት ከህግ ውጪ ተሰማርተው የተገኙ 20 የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው እደተሰረዘባቸው ተናግረዋል፡፡
ከውጪ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች ማበረታቻ እና ድጋፍ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኩል ይደረግላቸዋል ያሉት ሀላፊው ከድጋፉ ጎን ለጎን ቁጥጥር እንደሚደረግና አጥፍተው ሲገኙ ወዲያው እርምጃ እንደሚወሰደም መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i





Comments