የመኪና ባለቤት እናደርጋችኋለን በሚል የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት ባደረሱት የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ላይ ምርመራ አጣርቶ ለዐቃቤ ሕግ በመላክ ክስ መመስረቱ ተሰማ።
- Mar 28
- 3 min read
መጋቢት 19/2018
የመኪና ባለቤት እናደርጋችኋለን በሚል የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት ባደረሱት የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ላይ ምርመራ አጣርቶ ለዐቃቤ ሕግ በመላክ ክስ መመስረቱ ተሰማ።
ድርጅቱን ሲያስተዋውቁ የነበሩ ታዋቂ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸው ፍርድ ቤትም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም መፍቀዱ ተነግሯል ፡፡
ፊንቴክ ኢንቬስትመንት የግል ድርጅት መስራችና ባለቤቶች የሆኑት ዳንኤል ዮሃንስ ኢየሱስ እና ግርማይ ገ/ሚካኤል ይህደጎ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በመጠቀም ከ1200 በላይ ዜጎችን በማጭበርበር የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት በማድረሳቸው በ19 ዓይነት የተለያዩ ወንጀሎች ምርመራ አጣርቶባቸው ለዐቃቤ ሕግ በመላክ ዓቃቤ ሕግ ክስ መመስረቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስረድቷል።

መጀመሪያ ክሱ የቀረበው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ቢሆንም ምርመራው ውስብስብና ከፍተኛ ልምድ የሚጠይቅ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ በተደራጀ መልኩ መጣራት ስላለበት ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በማምጣት ምርመራው በስፋት ሲጣራ መቆየቱን ፖሊስ ጠቅሷል።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ተጎጂዎችን 50 በመቶ ቅድመ ክፍያ 950 ሺህ ብር በማስከፈል በ90 ቀናት ውስጥ የመኪና ባለቤት እንደሚያደርጓቸውና ቀሪ 950 ሺህ ብር ደግሞ ያለወለድ በ5 ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ የባንክ ብድር እንደሚያመቻቹላቸው በመግለጽ ዜጎችን በማጭበርበር ክፍያውን እንዲፈጽሙ አድርገዋል ሲል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መግለጫ ተናግሯል ።
ተጠርጣሪዎቹ ኅብረተሰቡን ለማሳመን 148 መኪኖች ከጅቡቲ በማስገባት 100 መኪኖች ለተወሰኑ ግለሰቦች እንዲከፋፈል በማድረግ እና ቀሪ 48 ዘመናዊ መኪኖችን መርጠው በድብቅ መሸጣቸውን እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ስለመግባታቸው ምንም አይነት መረጃና ማስረጃ ሳይኖር 350 መኪኖችን ከውጭ እንዳስገቡ በማስመሰል ኅብረተሰቡን ሲያጭበረብሩ እንደነበር ፖሊስ በምርመራው አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በተጨማሪም በጅቡቲ ወደብ ምንም ዓይነት መኪና ሳይኖር 400 መኪኖች ጅቡቲ ወደብ ላይ እንደቆሙና ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ እንዳሉ በማስመሰል ለተጎጂዎች ሐሰተኛ መረጃ መስጠታቸውን ፖሊስ ማረጋገጥ መቻሉን አስረድቷል ።
በመስቀል አደባባይ ከተለያዩ ቦታዎች መኪኖችን በትውስት በማሰባሰብ ሕዝብን በሚያሳስት መልኩ ድርጅቱ ከውጭ ሀገር ያስገባቸው መኪኖች እንደሆኑ በማስመሰል እና የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ከሆነው BYD ከተባለ የቻይና ካምፓኒ ጋር ምንም ዓይነት ውል ሳይኖራቸው ውል እንዳላቸው አድርገው የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ፖሊስ በምርመራ ደርሼበታለሁ ብሏል።

ተጠርጣሪ ዳንኤል ዮሃንስ ላይ ክስ ተመስርቶበት ማረሚያ ቤት ሆኖ ክሱን እንዲከታተል መደረጉንና ተጠርጣሪ ግርማይ ገ/ሚካኤልን ደግሞ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተናግሯል።

ግርማይ ገ/ሚካኤል የተባለው ግለሰብ ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ2010 የደቡብ አፍሪካ የዓለም የእግር ኳስ ሻምፒዮና ወቅት አስካሉካን በተባለ ድርጅት ስም ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄዳችሁ የዓለም ዋንጫ እንድትመለከቱ አደርጋለሁ በማለት ዜጎችን አጭበርብሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ካሰባሰበ በኋላ ተደብቆ ከሀገር በመውጣቱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በመተባበር ባደረገው ጠንካራ ክትትል ከተደበቀበት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ አድርጎ በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረጉን የወንጀል ሪከርዱ እንደሚያመላክት ፖሊስ አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በጅቡቲ ውስጥ አልፋቲዞ በሚል ስም ድርጅት በማቋቋም BYD ከተባለ የቻይና ካምፓኒ ጋር አብሮ ከሚሰራ ሌላ ድርጅት ጋር በመነጋገር 10 በመቶ ቅድመ ክፍያ በመክፈል የመጀመሪያዎቹን 148 መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተው እንደነበርና ተጨማሪ 188 መኪኖችን በተመሳሳይ 10በመቶ ቅድመ ክፍያ ለድርጅቱ በመክፈል መኪኖቹን ተረክበው ወደ ሀገር ውስጥ ሳያስገቡ ጅቡቲ ላይ እንዲሸጡ ማድረጋቸውንና በአጠቃላይ 336 መኪኖችን 10 በመቶ ጅቡቲ ለሚገኘው የቻይና ድርጀት በመክፈል ወስደው ቀሪ 90 በመቶ ክፍያ አለመፈፀማቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባደረኩት ምርመራ ደርሼበታለሁ ብሏል።

ከ1200 በላይ ተጎጅዎችን በማጭበርበር መዝግበው 95 ሺህ ብር ቅድመ ክፍያ፤ 285 ሺህ ብር የመንግስት ታክስ እንዲሁም 130 ሺህ ብር ለኤክትሪክ መኪና ቻርጀር ለማሰራትና ለባለሙያ በሚል ከእያንዳንዳቸው 1 ሚሊየን 365 ሺህ ብር መቀበላቸውን ተጠቅሷል፡፡

የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅትን ባልተገባና በተጋነነ መልኩ በማስተዋወቅ በህገወጥ መንገድ ከተሰበሰበው ገንዘብ ተጋሪ በመሆን የተጠረጠሩ ሰለሞን ቦጋለ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ አብርሃም ግዛው፣ ይገረም ደጀኔ፣ መንሱር ጀማል እና ካሊድ ናስር የተባሉ ታዋቂ አርቲስቶችና የማስታወቂያ ባለሙያዎችንም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ፍርድቤት በማቅረብ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸው ፍርድ ቤትም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም መፍቀዱ ተነግሯል ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በማጭበርበርና በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ (Money laundering) እና የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ጨምሮ በ19 የወንጀል ጉዳዮች በተጠረጠሩ የፊንቴክ ኢንቬስትመንት ድርጅት መስራቾችና ባለቤቶች እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸዉን ዕውቅናና ተቀባይነት በመጠቀም ሆነ ብለው የተጋነነ ማስታወቂያ በመንገር እና በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማሰራጨት ዜጎችን እንዲጭበረበሩ በማድረግ በሕገወጥ መንገድ ከተገኘዉ ገንዘብ እያንዳንዳቸዉ አሁን ባለዉ የገበያ ዋጋ ስምንት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቢ.ዋይ.ዲ ሶንግ ፕላስ የመኪና ስጦታ በመቀበል፤ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ (Money laundering) እና በዜጎች ላይ ከ1.7 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ በተጠረጠሩ አርቲስቶችና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ላይ የጀመረውን ምርመራ ይቀጥላል ተብሏል።





Comments