በሀገሪቱ ምን ያህል ቋንቋዎች እንዳሉ ከግምት በዘለለ ይታወቃል?
- 2 hours ago
- 1 min read
ሰኔ 18/2018
በኢትዮጵያ ቋንቋ ከማንነት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ቢሆንም፤ በሀገሪቱ ምን ያህል ቋንቋዎች እንዳሉ ከግምት በዘለለ ይታወቃል? ጥናትስ ተካሄዶበታል ወይ? ስንል ጠይቀናል፡፡
ቋንቋ በአብዛኛው ከማንነት ጋር ተያይዞ በሚነገርበትና የየቋንቋው ተናጋሪዎች አሁን አሁን በተሻለ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው በሚባልበት በዚህ ጊዜ ምን ያህል ቋንቋ እንዳለን አለመታወቁ ለጉዳዩ ተሰጥቶታል ከሚባለው ትኩረት ጋር የሚቃረን መሆኑን ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡
ተደጋግሞ እንደሚነገረው ከ80 በላይ ቋንቋዎች አሉ ቢባልም የሃገሪቱን ፖለቲካል ኢኮኖሚ የመወሰን አቅም የተሰጠው ቋንቋ በትክክል ቁጥሩ ምን ያህል ነው?
አንዱ ከሌላው በምን ይለያል? የየአካባቢውን ዘዬ ከዋናው ቋንቋ እንዴት ነው የምንለየው? የሚሉት ጥያቄዎች በስነ ልሳን ባለሙያዎች ዘንድ ያልተመለሱና ጥናት የሚያስፈልጋቸው ናቸው ያሉን በጉዳዩ ዙሪያ ሃሳባቸውን የሰጡን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የስነ ልሳን መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ዘላለም ልየው ናቸው፡፡
የፌድራል ሥርዓቱ ቋንቋ ላይ መሰረት ያደረገ እንደመሆኑ መጠኑን ከማወቅ ጀምሮ ባህሪያቸውን እስከ መለየት ያሉ ስራዎች በፖለቲከኞች መሰራት ነበረበት የሚሉት ፕሮፌሰሩ የሃገሪቱ የቋንቋ ፖሊሲ ዜጎች በቋንቋቸው መማርና ራሳቸውን ማስተዳደርና ማሳደግ እንዲችሉ እድል መስጠቱ መልካም ነው፤ ነገር ግን ተለይቶ አለመታወቁ ማንነታቸው የማታወቅ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲኖሩና በሌሎች የመዋጥ እጣ እንዲገጥማቸው እንደሚደርግም ያነሳሉ፡፡
ይህ በሃገር ውስጥ የሚነገር ቋንቋን ምን ያህል እንደሆነ አለማወቅ በኢትዮጵያ ብቻ ያለ ችግር አይደለም በማለት ታንዛኒያንና ናይጄርያን በምሳሌነት የሚጠቅሱት የስለ ልሳን መምህሩ ፕሮፌሰር ዘላለም በእነዚህም ሃገራት ምን ያህል ቋንቋዎች እንደሚነገሩ የሚገለፀው በግምት ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በተለምዶ ቀበሊኛ እየተባለ የሚጠራው አንድን ቋንቋ እንደየአካባቢው ዘዬ መናገር የትኛው ዘዬ ነው ትክክል፤የቋንቋው ባለቤትነት ለማን ይሰጥ የሚለውም ለባለሙያዎች በጣም ፈታኝ ነው፤ እንደ ኖርዌይ ያሉ ሃገራትም የሚፈተኑበት ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በ47 ዩንቨርሲቲዎች እየከወነ ያለውና አሁን የጥናቱ 90 በመቶ ተጠናቅቋል የተባለው የሃገር በቀል እውቀቶች ጥናት እግረ መንገዱን ቋንቋዎችንም ያካትታል ይሁንና ጉዳዩ ራሱን ችሎ መጠናት ይኖርበታል ብለውናል ባለሙያው፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….
ምንታምር ፀጋው





Comments