top of page

የሐምሌ 28 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

  • 1 day ago
  • 2 min read


አለም አቀፉ ዕውቅና አለው የሚባለው የየመን መንግስት ወታደሮቼ በጣም ብዙ የሁቲ ታጣቂዎችን ገደሉ አለ፡፡


በደፈናው በጣም ብዙ የሁቲ ታጣቂዎችን ሙት እና ቁስለኛ አድርገናል ቢልም ብዛታቸውን በአሃዝ ይሄን ያህል ነው እንዳላለ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


የሁቲ ታጣቂዎቹ የተገደሉ በደቡባዊ ምዕራቧ ታይዝ ግዛት በተካሄዱ ውጊያዎች ነው ተብሏል፡፡


በጣም ብዙ ታጣቂዎቻቸው ተገድለዋል ስለመባሉ ሁቲዎቹ ምንም ዓይነት አስተያየት እንዳልሰጡ ተጠቅሷል፡፡


አለም አቀፍ እውቅና አለው የሚባለው የየመን መንግስት መቀመጫው በደቡባዊቱ የወደብ ከተማ ኤደን ነው፡፡


የኢራን ሽርካዎች ናቸው የሚባሉት ሁቲዎቹ ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ አብዛኛውን የየመን ሰሜናዊ ክፍል ሲያስተዳድሩ ከ10 አመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡



ሁለት እስራኤላዊያን ሚኒስትሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በማንኛውም ሁኔታ በጋዛ ሰርጥ አለም አቀፋዊ አረጋጊ ሀይል መስፈሩን ሊፈቅዱ አይገባም አሉ፡፡


በጋዛ አለም አቀፍ አረጋጊው እንዳይሰፍር ጥያቄውን ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች እና የሰፈራ ሚኒስትሩ ኦሪት ስትሮክ እንደሆኑ ታይምስ ኦፍ ኢዝራኤል መዘገቡን አናዶሉ ፅፏል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ለጋዛ ሰርጥ ሰላም ያቀረቡት ባለ 20 ነጥቦች እቅድ በሰርጡ አለም አቀፍ አረጋጊ ሀይል እንዲሰፍር የሚጠይቅ ጭምር እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡


ባለፈው ሳምንት የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ አረጋጊ ሀይሉ በጋዛ እንዲሰፍር ውሳኔ አሳልፏል ተብሏል፡፡


ሁለቱ ሚኒስትሮች የአረጋጊ ሀይሉን መስፈር የተቃወሙት የፍልስጡማውያኑ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት (ሐማስ) ትጥቅ የማስረክበው በሰርጡ ለሚሰፍረው አለም አቀፋዊ አረጋጊ ሀይል ነው ማለቱን ተከትሎ ነው፡፡


ሁለቱ እስራኤላዊያን ሚኒስትሮች የአለም አቀፉን አረጋጊ ሀይል በጋዛ መስፈር መቃወማቸው የሐማስን ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችል ተገምቷል፡፡



የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ለጦርነቱ ማስቆሚያ በሚደረገው ድርድር ከመስማማት በስተቀር እድሏ በጣም ጠባብ ነው አሉ፡፡


ትራምፕ ኢራን ካልተስማማች ሙሉ በሙሉ እጅ መስጠት ሊያስከትልባት ይችላል ማለታቸው አልጀዚራ ፅፏል፡፡


ትራምፕ ኢራን አመነችም አላመነችም ይሄ መሆኑ አይቀርም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ወደ አዲሱ ዛቻ የተመለሱት ኢራንን ማጥቃቴን የገታሁት ኢራንን ጨምሮ የአካባቢው አገሮች ስለተማፀኑኝ ነው ካሉ በኋላ ነው፡፡


የኢራን አብዮታዊ ዘብ የምድር ጦር አዛዥ ሞሐማድ ካራሚ ጦራቸው የመጣውን ሁሉ እንደ አመጣጡ ለመመለስ በሙሉ ተጠንቀቅ ላይ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የጦር አዛዡ በሁሉም መስክ ተዘጋጅተን እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡


የኢራኑ ጦርነት ቆመ ከመባሉ የማገርሸት አባዜ እንደተጠናወተው መረጃው አስታውሷል፡፡


ትራምፕ ለኢራን ይሄ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያዬ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡



ሰሞኑን በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ፈላጊዎች ባህሩን በመዋኘት ከሞሮኮ ተሸግረው ወደ ሰሜን አፍሪካዋ የስፔን ሴኡታ ግዛት የገቡት በየማህበራዊ ገፁ በተናፈሰው ሐሰተኛ መረጃ ተገፋፍተው ነው ተባለ።


ስደተኞቹ ከሞሮኮ ባህሩን በዋና አቋርጠው ከመግባታቸው አስቀድሞ እንደ ፌስ ቡክ እና ኢንስታግራም ባሉ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ስፔን የሴኡታን ድንበር ከፍታለች የሚል ሰሐተኛ ወሬ በስፋት ተናፍሶ እንደነበር በአሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


ባለፈው ሳምንት በ24 ሰዓታት ጊዜ ብቻ ከ60 ሺህ በላይ ጥገኝነት ፈላጊዎች ወደ ሴኡታ ገብተው ነበር፡፡


ባህርን ዋኝተው በማቋረጥ ወደ ሴኡታ ለመግባት ከሞከሩት መካከል ከ80 የማያንሱት በባህር ላይ መሞታቸው ተጠቅሷል፡፡


ስፔን በሴኡታ የፀጥታ ሀይሏን እያጠናከረች ነው፡፡


ዋኝተው ወደ ሴኡታ ከገቡት ጥገኝነት ፈላጊዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ወደተነሱባት መሮኮ እንዲመለሱ መደረጉ ታውቋል፡፡


አሁንም በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ፈላጊዎች ዳግም ባህሩን በዋና አቋርጠው ወደ ሴኡታ የመግባት ፍላጎት እንዳቸው ተሰምቷል፡፡


የኔነህ ከበደ

Recent Posts

See All
እንደ ጣና ያሉ ሀይቆችና የውሃ አካላት ላይ ተንሰራፍቶ ከሚገኘው የእምቦጭ አረም የነዳጅ ምርቶችን ለማምረት ይሰራል ከተባለ ከአምስት አመት በላይ ሆኖታል።

ሐምሌ 29 2018 እንደ ጣና ያሉ ሀይቆችና የውሃ አካላት ላይ ተንሰራፍቶ ከሚገኘው የእምቦጭ አረም የነዳጅ ምርቶችን ለማምረት ይሰራል ከተባለ ከአምስት አመት በላይ ሆኖታል። ይተገበራል በተባለው ፕሮጀክትም ነጭ ጋዝ፣ ቤንዚን ፣ኪሮሲን፣ የአውሮፕላን ነዳጅ እና ሚቴን ማምረት የሚለው ይገኝበታል ። ተረፈ ምርቱ ከነዳጅ

 
 
 
ኢትዮጵያ ሁለት ዓይነት የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን እንደምትከተል ይነገራል::

ሐምሌ 29 2018 ኢትዮጵያ ሁለት ዓይነት የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን እንደምትከተል ይነገራል:: ይህም የከተማ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትና የገጠር የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ተብሎ እንደሚጠራም ሰምተናል:: በዚህም የከተማው በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የገጠሩም እንዲሁ በሌላ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እየተመራ ይገኛል

 
 
 
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page