የህብረት ሥራ ማህበራት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ወደ ግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመራ፡፡
- sheger1021fm
- 2 hours ago
- 2 min read
ጥር 14/2018
የህብረት ሥራ ማህበራት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ወደ ግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመራ፡፡
ከዚህ ቀደም በተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ የሚደረገው ዓመታዊ ኦዲት አሁን የህብረት ሥራ ማህበራት በራሳቸው ወጪ ኦዲት እንዲደርጉ የሚስገድደው የህብረት ሥራ ማህበራት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ፓርላማው ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መራ፡፡
ማሻሻያ አዋጁ የህብረት ስራ ማህበርት ካፒታላቸውን ለማሳደግ አባል ላልሆኑ ሰዎች የአክሲዮን እጣ እንዲሸጡ ይፈቅዳል፡፡
ዛሬ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባው ኦዲትን በተመለከተ በፓርላማው ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበረውን የህብረት ስራ ማህበራት አዋጅ መርቶታል፡፡
ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በስራ ላይ ባለው አዋጅ ማህበሩ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የማንኛውንም ህብረት ስራ ማህበር ሂሳብ ራሱ ማለትም ተቆጣጣሪው መስሪያ ቤት እራሱ አልያም በሚወክለው ሰው ኦዲት ያስደርጋል የሚለው አንቀጽ ሙሉ ተሰርዞ ማህበራት እራሳቸው ኦዲት እንዲያስደርጉ ያስገድዳል፡፡
የህብረት ሥራ ማህበራት ሂሳብ ኦዲት የሚደረገው በህብረት ሥራ ሊግ፣ በኦዲት ሙያዎች በተደራጀ የኅብረት ሥራ ማህበር ወይም ህጋዊ የኦዲት ፈቃድ ባለው ሰው መሆን እንዳለበት የዘረዘረው ረቂቁ ነገር ግን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተቆጣጣሪው በልዩ ሁኔታ የኅብረት ሥራ ማህበራት ሂሳብ ኦዲት ማድረግ እንደሚችል ደንግጓል፡፡
ሌላው በረቂቅ አዋጁ እንዲሻሻል የቀረበው የህብረት ስራ ማህበርት ካፒታላቸውን ለማሳደግ አባል ላልሆነ ሰዎች የአክሲዮን እጣ እንዲሸጡ መፍቀድን የተመለከተ ነው፡፡
በዚህም መሰረት ማንኛውም የህብረት ሥራ ማህበር ካፒታል ለማሳደግ አባል ላልሆነ ሰው ዕጣ መሸጥ እንደሚችል የሚደነግገው ረቂቁ፤ ሆኖም የሚሸጠው ዕጣ ከታወጀው ጠቅላላ ዕጣ ከ10 ከመቶ መብለጥ እንደሌለበት ገደብ ያስቀምጣል።
የእጣ ባለቤቶችን መብት እና ግዴታን በተመለከተ ደግሞ የህብረት ሥራ ማህበሩ ከከሰረ የኪሳራው ተጋሪ ሊሆን አይችልም እንዲሁም የመምረጥ እና የመመረጥ መብት እንደሌለው ረቂቁ ደንግጓል፡፡
በተጨማሪም የኅብረት ሥራ ማህበራት በትራንስፖርት፣ በመዓድን፣ በኢነርጂ አቅርቦት፣ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ እንዲሳተፉ ይፈቅዳል ፡፡
ስራ ላይ ባለው አዋጅ ግን እነዚህ ማህበራት በእነዚህ መስኮች ላይ እንዲሳተፉ የሚፈቅድም ሆነ የሚከለክል ድንጋጌ የለውም፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በስራ ላይ ያለው አዋጅ በዓመት ቢያንስ ሁለተ ጊዜ ስብሰባ እንዲደርጉ የሚስገድደው አንቀጽ አሁን ወደ አንድ እንዲሻሻል ይጠይቃል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…..
YouTube : https://url-shortener.me/2DTR
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://url-shortener.me/2DTY
WhatsApp :https://url-shortener.me/2DU0
X : https://x.com/shegerfm?s=2
Website፡ https://www.shegerfm.com/
LinkedIn :https://url-shortener.me/2DU8
Tiktok : https://url-shortener.me/2DUB
Instagram : https://url-shortener.me/2DUD











Comments