top of page

የሀይማኖት ምልክቶችን የሚያንቋሽሹ ሰዎች በህግ እንዲጠየቁ ካልተደረገ ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተነገረ

  • sheger1021fm
  • 5m
  • 3 min read

ጥቅምት 28 2018


የሀይማኖት ምልክቶችን የሚያንቋሽሹ እና ንፁሀን የሚገድሉ ሰዎች በህግ እንዲጠየቁ ካልተደረገ ለከፋ ግጭት መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተነገረ።


በአደባባይ፣ በጎዳናዎች የሚደረጉ ስብከቶችን ጨምሮ የሀይማኖት ዶግማዎችን የሚያንቋሽሹ እና የሚያነውሩ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚረዳ ስርዓት ለማበጀት ወይይት ተጀምሯል ተብሏል።


የአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ የከተማዋ ኮሚኒኬሽን ጉዳይዎች ቢሮ፣ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ከሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን በሰላም ጉዳይ ላይ በትናንትናው እለት ተወያይተዋል።


አንድ የውይይቱ ተሳታፊ ህጻናትን ጨምሮ ንጹሃን እየተገደሉ ነው፡፡ ይህን ወንጅል የሚፈጽሙ አካላት ለምንድነው በህግ የማይጠየቁት፣ መቼስ ነው የሚቆመው ሲሉ ጠይቀዋል።


ንጹሃን እየተገደሉ እስከመቼ ነው የምንቀጥለው? ሰሞኑን እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችስ መቼ ነው መላ የሚያገኙት? ለምንስ ነው ከምንጩ ማድረቅ ያልተቻለው ሲሉም አከለዋል። አንዱ ሲሞት ሃዘናችን ለምንድነው የጋራ የማይሆነው? ለምንስ ነው መርጠን የምናዝነው? ሲሉ ጠይቀዋል።


መጋቢ አብይ ታደለ የተባሉ ሌላ ተሳታፊ በበኩላቸው የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን አንዱ አላማቸው የራሳቸውን የእምነት ዶግማ ማስተማር እንደሆነ አስታውሰዋል። ሰላም ለማስተማርም ቢሆን ግን ድርሻቸው ከፍተኛ ነው ምክንያቱም ከፍተኛ ተከታይ ስላላቸው ብለዋል።


ነገር ግን በምንሰብክበት ወይም በምናስተምርበት ወቅት የሌላውን ሃይማኖት ልክ አይደልም፡፡ የእኛ ነው ትክክለኛው መንገድ እያልን ነው የምናስተምረው ይህ እንዳያጋጭ የቱ ጋር ነው ሚዛን መጠበቅ ያለብን? ሲሉ ጠይቀዋል።


የከተማዋ ኮሚኒኬሽን ጉዳይዎች ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዘውዱ ከበደ በከተማዋ በሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ስም ፍቃድ ወሰደው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሚዲያዎች መኖራቸውን ተናግረው ከእነዚህ ውስጥ ግን የቱ ነው በአግባቡ ስራውን እያሰራ ያለው የሚለውን መለየት አሰፈላጊ ይሆናል ብለዋል።


እነዚህ መገናኛ ብዙሃን እንደ ሃይማኖታቸው አስተምህሮ እየሰሩ ነው ወይ? ተከታዮቻቸውን ማስተማር ችለዋል ወይ? እንዲሁም ወደ አንድነት እና ሰላም ህዝቡን ማምጣት ችለዋል ወይ? ብለን ብንጠይቅ ያለ ምንም ጥርጥር አብዛኞቹ ከዚህ በተቃራኒ የቆሙ ናቸው ሲሉ አስረድተዋል።


የሃይማኖት አስተማሪዎች ስለ ሃይማኖታቸው ሲያስተምሩ አንዱ የሌላውን ልክ አደለም ብሎ ያስተምራል በዚህ እንዴት ነው ሚዛኑን የምንጠብቀው በሚል ከመጋቢ አብይ ለቀረበላቸውጥያቄም አቶ ዘውዱ ሲመልሱ የራስን አስተምህሮ ማስተማር እንጂ ስሌላው አሉታዊ ነገር ማስተላለፍ ተገቢ አይደለም ብለዋል።


የእኔ ልክ ነው የእገሌ ደግሞ ስህተት ብሎ በመገናኛ ብዙሃን ማስተላለፍ ለግጭት ሊዳርግ የሚችል ተግባር መሆኑን ያስረዱት ምክትል ሃላፊው የሃይማኖት አባቶች ማስተማር ያለባቸው አንዱ ከአንዱ የሚለይበትን ነው መሆን ያለበት ብለዋል። የሌላውን መንቀፍ እና ማንቋሸሽ ለግጭት የሚዳርግ መሆኑ መታወቅ አለበት ሲሉም አክለዋል።


የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጻሃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በበኩላቸው አንድ ሰው የቱንም ሃይማኖት ቢከተል ሰው በመሆኑ ብቻ ሊከብር እንደሚገባው መታወቅ አለበት ሲሉ ተናግረዋል። መርጦ ማልቀስ አያስፈልግም ያሉት ጽሃፊው ሰው ከተጎዳ ኦርቶዶክስም፣ ሙስሊሙም ሆነ ፕሮቴስታንቱ የኔ ነው በሎ ማሰብ ተገቢ እና ጤነኛ አስተሳሰብ ነው ሲሉ አስረድተዋል።


ለሰው ክብር መስጠት ወሳኝ ነገር ነው ያሉት መጋቢ ታምራት በተለይ ከሃይማኖቶች የሚጠበቀው ለሰው ክብር መስጠት እና ሰላም ነው ብለዋል።


የጎዳና ስብከት እና የጥላቻ ንግግም ቢሆን መላ ሊበጅለት ይገባል የሚሉት መጋቢ ታምራት የአንድን እምነት ቀኖና ማንቋሸሽ፣ ሃይማኖታዊ ምልክትን ማንቋሸሽ አለ እነዚህን ነገር በጊዜ መፍታት ካልቻልን ነገ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።


የአዲስ አበባ ሰለም እና ጸጥታ ቢሮ በበኩሉ ሰላም ላይ መስራት አለብን ብሏል።


የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራ መስራት አለብን እንዲሁም የህግ ማሻሻያ የሚፈልጉ ጉዳዮችንም ተወያይቶ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።


የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ረታ የህግ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ግብዓት መሆን የሚችሉ ነገሮች መስጠት ደግሞ ከእናንተ ይጠበቃል ሲሉ ተወያዮቹን ጠይቀዋል።


የከተማዋ ኗሪዎች በጎዳናዎች፣ በአደባባዮች እና በንግድ ቦታዎች ሳይቀር እየተጎተትን እንሰበካለን የሚል ቅሬታ በየጊዜው ያቀርባሉ ያሉት ምክትል ሃላፊው ይህን መከልከል የምንችለው በህግ እና በአዋጅ ነው ለዚህ የሚረዳ ሃሳብ ደግሞ ከእናንተ እንፈልጋለን ብለዋል።


በመጨረሻም የሃይማኖት ተቋማት ከሚያራርቁ እና ግጭት ቀስቃሽ ድርጊቶች እራሳቸውን እንዲጠብቁ ጠይቀዋል።


አቶ ብርሃኑ በከተማዋ ከኢትዮጵያዊያን ባህል፣ ወግ እና እምነት የወጡ ለሚዲያ መግለጽ የማይሆኑ ድርጊቶች በርክተዋል፤ ግብረ ገብ ላይ እባካችሁ ስሩ ሲሉ ተማጽነዋል። ትውልዱ ወዴት እየሄደ ነው ሱሊ የጠየቁት ሃላፊው የሃይማኖት ተቋማት እና ሚዲያ ትውልዱ ላይ ካልሰራ እውነተኛ ማንነታችን ይጠፋል ብለዋል።


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ……


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page