ከፍተኛ የት/ት ተቋማት በ4መመዘኛዎች 60 ከመቶ በላይ ውጤት ካመጡ ወደ ራስ ገዝነት ሽግግር እንዲያደርጉ የሚያዝዝ መመሪያ
- 5 hours ago
- 2 min read
ሰኔ 23/2018
ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአራት መመዘኛዎች ከ60 ከመቶ በላይ ውጤት ካመጡ ወደ ራስ ገዝነት ሽግግር እንዲያደርጉ የሚያዝዝ መመሪያ አወጣ።
መመሪያው ዩኒቨርስቲዎች ራስ ገዝ ለመሆን በውስጣቸው የያዙትን የመምህራን የትምህርት ደረጃ መስፈርት የሚያደርግ ነው።
ትምህርት ተቋማቱ በአስተዳዳር፣ በፋይናንስ፣ በሰው ኃይል አደረጃጀትና በአካዳሚክ አምዶች በተዘጋጀው መመዘኛ መሰረት ከ60 በመቶ በላይ ውጤት ካመጡ ወደ ራስ ገዝነት ሽግግር እንዲጀምሩ የትምህርት ሚኒስቴር ይፈቅዳል።
መመሪያው የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች እና መመዘኛዎች ለመወሰን የወጣ ነው።
በዚህም መሰረት የአስተዳደር አምድ 30 ከመቶ፣ ፋይናንስ 20 ከመቶ፣ ሰው ሃይል 15 እና አካዳሚክ አምድ 35 ከመቶ ይይዛሉ።
በአስተዳደር አምድ ስር ተቋማዊ መዋቅር እና የሰው ኃይል አደረጃጀት ፣ ከፍተኛ በየደረጃው የተለየ የተቋም የውሳኔ አሰጣጥ፣የኃላፊነትና ተጠያቀነት መመሪያ ያዘጋጀ መሆኑ፣ተቋማዊ የዲጂታል መሰረተ ልማት፣ የመረጃ ቋት መገንባቱ፣ የሚሰጡ አገልግሎቶች አውቶሜት ማድረግ መቻሉ፣ የስማርት ክፍሎችን ብዛት 15 ከመቶ ማድረሱ እና ሎሎች መስፈርቶች በዚህ ዓምድ ስር ከ 2 እስከ 4 ነጥብ የሚያሰጡ መሆናቸው ተዘርዝሯል።

ሦስት ተከታታይ የቅርብ ዓመታት ኦዲት ያስደረገ እና የኦዲት አፈጻጸም ግምገማ ውጤቱ ንጽህ እና ከተወሰነ በስተቅር ችግር የሌለበት ከሆነ፣ባለፉት ሦስት ተከታታይ አመታት ከጠቅላላ በጀቱ 15 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ሀብት ያመነጨ ከሆነ፣የገቢ ብዝሃ ምንጮች አሰራር ስርዓት የተዘረጋ ከሆነ፣የሀብት አመዳደብ ቀመር መመሪያ፣ የውስጥ ኦዲት ቁጥጥር መመሪያ፣ የሀብት አስተዳደር መመሪያ፣ የፋይናንስ ፖሊሲ መመሪያና የአሰራር ማንዋሎች ያዘጋ እና ሌሌሎች መስፈርቶችን ካሟላ ደግሞ በፋይናንስ አምድ ስር ከ1.5 እስከ 3 ነጥብ የሚያሰጡ መስፈርቶች ናቸው።
በሰው ሃይል አምድ ስር ደግሞ የተቋሙ አካዳሚክ የሰው ሀይል የትምህርት ደረጃ ስብጥር ተዘርዝሯል።
የመጀመሪ ዲግሪ ከመቶ ዜሮ፣ ሁለተኛ ዲግሪ 60 ከመቶ፣ ሶስተኛ ዲግሪ 40 ከመቶ ያደረሰ ከሆነ፤የተቋሙ አካዳሚክ የሰው ሃይል የአካዳሚክ ማዕረግ ስብጥር ደግሞ ሌክቸረር 46 ከመቶ፣ ረዳት ፕሮፌሰር 31 ከመቶ ፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር 20 ከመቶ፣ ፕሮፈሰርና ከዚያ በላይ 3 ከመቶ መሆን አለበት ይላል።
በተጨማሪም በየደረጃ ላሉ አመራርና ሠራተኞች የጥቅማ ጥቅም፣ ምቹ የስራ ከባቢ፣ የመኖሪያ ቤት እና የተሻለ የአፈጻጸም ማበረታቻ ለሟሟላት የሚያስችል መመሪያ ያዘጋጀ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመረ መሆን እና ሌሎች መስፈርቶች በሰው ሃይል አምድ ስር ከ1 እስከ 2 ነጥብ የሚያሰጡ መስፈርቶች ናቸው።
በአካዳሚክ አምድ ስር ደግሞ ከተቋሙ ተልዕኮ ልየታና ትኩረት መስክ ፕሮግራሞች አንጻር ቢያንስ 5 ከመቶ አለም አቀፍ እውቅና ያገኘ፣ተቋሙ ላለፉት ተከታታይ ሶስት ዓመታት በሁሉም ትምህርት ፕሮግራሞች የውስጥ የጥራት ኦዲት ያደረገ፣ መሆን እንዳለበት ዘርዝሯል።
እንዲሁም የአእምሯዊ ንብረት መብት ፖሊሲ እና መመሪያዎች ያዘጋጀ፣ በተቋም ደረጃ ከተልዕኳቸውና ከትኩረት መስካቸው አንፃር 5 እና ከዛ በላይ የአእምሯዊ ንብረት መብት ያገኘ ፣ዩኒቨርሲቲው 70 ከመቶ እና ከዚያ በላይ የቤተ መፃሀፍት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ያደረገ መሆን እንዳለበት ተጠቁሟል።
በሁሉም ፕሮግራሞች ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የመውጫ ፈተና የወሰዱ ቅድመ-ምረቃ ተማሪዎችን 80 እና ከዚያ በላይ ያሳለፈ የሚሉ መስፍርቶች ደግሞ በአካዳሚክ አምድ ስር ከ1 እስከ 4 ነጥብ የሚያሰጡ መሆናቸው ተዘርዝሯል።
መመሪያው አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን በ23 ገጽ የተሰናዳ ነው።
በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ-ገዝ አስተዳደር ለመሸጋገር ማሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን በተመለከተ ደግሞ ጠንካራ የፋይናንስ የውስጥ የቁጥጥር ሥርዓት የገነቡ፣ ውጤታማ የሀብት አጠቃቀም ልምድ ያላቸው መሆን አለባቸው ይላል መመሪያው።
የሽግግር ዝግጁነቱን ለመገምገም ትኩረት የሚደረግባቸው ነጥቦችን ሲዘረዝር ደግሞ ውጤታማ የምርምር፣ የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስርዓት ከዘረጋ፣የአደጋ ስጋትና ዝግጁነት ስርዓት ከፈጠረ የሚሉት በሰነዱ ሰፍረዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የሚደረግ ግምገማን በተመለከተ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ-ገዝነት የሚያደርጉትን ሽግግር መወሰን የሚያስችለውን ግምገማ ለማካሄድ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ ለተቋሙ ማሳወቅ እንዳለባቸው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በአራቱ አምዶች መሰረት የትምህርት ሚኒስቴር የመንግስት ዩንቨርስቲዎችን ይገመግማል፣ በግምገማ ውጤቱ መሰረት 60 ከመቶ እና ከዛ በላይ ያገኘ ዩኒቨርሲቲ ወደ ራዘ-ገዝ ዩኒቨርሲቲነት የሚያሸጋግረውን የሚፈቅድ የማቋቋሚያ ደንብ ያዘጋጃል፤ በተደነገገው መሰረት መስፈርቱን ላስመዘገበ ተቋም የራስ ገዝነት ሽግግር ሂደት እንዲጀምር ፈቃድ ይሰጣል ይላል።
ከመስፈርቱ ዝቅ ያለ ውጤት ላስመዘገቡ ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር የግምገማውን ማሻሻያ ዝርዝር መግለጫ ለዩኒቨርሲቲው እና ለቦርድ በማቅረብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ድጋሚ እንዲያመልክቱ ያደርጋል ተብሏል።
ያሬድ እንዳሻው




Comments