top of page

ከማረሚያ ቤት በሮቶ የሚወጣ ቆሻሻ አስመስለው የህግ ታራሚዎችን ያስመለጡ የማረሚያ ፖሊስ አባላት መቀጣታቸው ተነገረ፡፡

  • 2 hours ago
  • 1 min read

የካቲት 25/2018


ከማረሚያ ቤት በሮቶ የሚወጣ ቆሻሻ አስመስለው የህግ ታራሚዎችን ያስመለጡ የማረሚያ ፖሊስ አባላት መቀጣታቸው ተነገረ፡፡


ይህንን የሰማነው ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ነው፡፡


ድርጊቱ ግን ግላዊ ጥቅማቸውን በማስቀደም ከህግ ታራሚዎች ጋር ቀድመው ተመሳጥረው ለማስጠፋት ዘዴ በዘየዱ የማረሚያ ፖሊስ አባላት ተፈፅሟል ሲልም ኮሚሽኑ አክሏል፡፡


በእርምት ላይ ይገኙ የነበሩት 1ኛ የህግ ታራሚ ቢኒያም ካህሳይ ገብሩ እና 2ኛ የህግ ታራሚ ዳንኤል ጎይቶም ተስፋዬ እየታረሙ ከሚገኙበት የከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ከሚኖሩበት ዞን ውጥተው በመጥፋታቸው ባደረግሁት ክትትል እና ማጣራት ነው ያስመለጧቸው አጃቢ የፖሊስ አባላት እንደሆኑ ደርሼበታለሁ ብሏል ኮሚሽኑ፡፡



ሁለቱ የህግ ታራሚዎች ለመጥፋት ይመቸናል ያሉትን ሃሳብና የስራ ቦታ ለአጃቢ የፖሊስ አባላት ቀድመው አሳውቀዋል፤ ፅዳት የሚያፀዱ ሌሎች ታራሚዎች ከግቢ የሚወጡ ተረፈ ምርቶችንና ቆሻሻዎችን ማጠራቀሚያ ሮቶ ውስጥ በመጨመር እንዲሁም ታራሚዎችን ደግሞ ቆሻሻ በማስመሰል እንዲያወጧቸው የማምለጫ መንገዳቸውን እንደዘየዱ አብራርቷል፡፡


ቀጥሎም ወደ ማረሚያ ግቢ ቆሻሻ ለመጫን በሚመጣው ተሸከርካሪ ውስጥ እንደቆሻሻ ተጭነው እንዲወጡ አመቻችተዋል ብሏል፡፡


የከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል በወቅቱ 8 የሚሆኑ የዞን፣ የበር ዘብ ተረኛ እና አጃቢ ፖሊሶችን በቁጥጥር ስር በማዋል በአካባቢው ለሚገኘው ለገላን አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አሳልፎ በመስጠት የገላን ፖሊስ ጣቢያም አስፈላጊውን ማጣራትና ምርመራ በማድረግ ክሱን አደራጅቶ ለአቃቢ ህግ አቅርቧል ተብሏል፡፡


ዓቃቤ ህግም ተገቢውን የሰነድና የሰው ማስረጃ በማጠናቀር ክስ መስርቶ የክስ ሂደቱን ሲከታተል የቆየው የኦሮሚያ ልዩ ዞን የገላን ከተማ ፍርድ ቤት የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት 1ኛ ሳጅን አደም ሽብሩ 2ኛ ም/ሳጅን መንገሻ ደገፋ 3ኛ ረዳት ሳጅን ልጃለም ተሜ የተባሉ የማረሚያ ፖሊስ አባላት ላይ የ1 አመት ፅኑ እስራትና እያንዳንዳቸው ላይ የ1000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል ሲል የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ተናግሯል፡፡


ማንያዘዋል ጌታሁን

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page