እንባ ጠባቂ ጠቋም ባለፉት 11 ወራ በድምሩ 44,900 በላይ ሰዎች የአስተዳደር በደል ተፈፅሞብናል በማለት አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ተናገረ፡፡
- 20 hours ago
- 2 min read
ሰኔ 18/2018
የህዝብ እንባ ጠባቂ ጠቋም ባለፉት 11 ወራ በድምሩ 44,900 በላይ ሰዎች የአስተዳደር በደል ተፈፅሞብናል በማለት አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ተናገረ፡፡
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዛሬ ለፓርላማ እያቀረበ የሚገኘው የ11 ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ሰነድ በለፉት 11 ወራት 1715 አቤቱታዎች መቀበሉን ይፋ አድርጓል፡፡
ከአቤቱታ አቅራቢዎች ውስጥ ከ17,000 በላይ የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ ከ7,900 በላይ ሚሆኑት ሴቶች ቀሪው ከ19,900 በላይ የሚሆኑት በጾታ ያልተለዩ በጥቅሉ ወደ ከ44,900 በላይ ሰዎች በደል ተፈጽሞብናል ብለው ቅሬታ ማቅረባቸውን ተቋሙ አስረድቷል፡፡
ከቀረቡ አቤቱታዎች መካከል 1,437 አቤቱታዎች በመንግስት ተቋማት ላይ የቀረቡ ናቸው፡፡
በግል ድርጅቶች ላይ የቀረቡት 278 ብቻ መሆናቸው ታውቋል፡፡

አቤቱታዎቹ በዘርፍ ሲዘረዘሩ ደግሞ ስራ 306 ጡረታ፣ 86 ይዞታ፣ 408 አገልግሎት አለማግኘት፣ 452 የካሳ ጥያቄ፣ 197 ትምህርት፣ 24 የመረጃ ጥያቄ እና 8 ልዩ ልዩ ጉዳዮችን የሚመለከቱ 234 መሆናቸውን የጠቋሙ የሪፖርት አስረድቷል፡፡
በአስራ አንድ ወራት ውስጥ 792 አቤቱታዎች ተቀባይነት አግኝተው ለምርመራ እንደተመሩ ያስረዳው እንባ ጠባቂ ተቋም ከ2017 በጀት ዓመት የዞሩ 282 መዝገቦችን ጨምሮ በድምሩ 1074 መዝገቦች ላይ ምርመራ ተከናውኖ 68 የሚሆኑት በቅድመ ምርመራ መፍትሄ እንዳገኙ አስታውሷል፡፡
231 መዝገቦች ደግሞ በደል አለመኖሩ ተረጋግጦ ውሳኔ የተሰጣቸው ናቸው፤ በደል መፈጸሙ ተረጋግጦ በድርድር መፍትሄ የተሰጣቸው መዝገቦች ደግሞ 164 ናቸው ተብሏል፡፡
168 መዝገቦች በደል መኖሩ በምርመራ ተረጋግጦ መፍትሄ ሃሳብ እንደሰጠባቸው፣ 180 መዝገቦች በአቤቱታ አቅራቢዎች ጥያቄና በተለያዩ ምክንያቶች መቋረጣቸው በድምሩ 811 መዝገቦች እንደተቋጩ ተዘርዝሯል፡፡
ቀሪው 263 መዝገቦች ምርመራቸው ባለመጠናቀቁ በሂደት ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በ168 መዝገቦች ላይ የመፍትሄ ሀሳብ የተሰጠ ሲሆን ከ2017 በጀት ዓመት ሳይፈፀሙ ከዞሩ 63 መዝገቦች ጋር በድምሩ 231 መዝገቦች ላይ የአፈጻጸም ክትትል ተደርጎ በ123 መዝገቦች ላይ የተሰጠው የመፍትሄ ሀሳብ የተፈፀመ ሲሆን 14 መዝገቦች ላይ 4 የመፍትሄ ሀሳቡን ላለመፈፀም በቂ ምክንያት የቀረበ በመሆኑ መቋረጡን አስረድቷል፡፡
94 መዝገቦች ምክረ-ሃሳቦችን ያለመፈፀምና የዘገዩ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ተቋሙ የአስተዳደር በደል ምርመራ ሥራ በማስረጃ አሰጣጥም ሆነ በማስፈፀም ሂደት ለመተባበር ፍቃደኛ ባልሆኑ 30 የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ክስ መስርቶ 10 ተቋማት እንዲፈፅሙ የተደረገ ሲሆን 20 መስሪያቤቶች ደግሞ ጉዳዮች በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡
ውሳኔ እንዲያገኙ ከተደረጉ መዝገቦች መካከል 82 ሰራተኞች ወደ ስራ እንዲመለሱ ተደርጓል፣ከ1ሺ300 በላይ ሰራተኞች የደረጃ ዕድገትና ፣ጥቅማጥቅም እና ደመወዝ እንዲከፈላቸው ተደርጓል ይላል ሪፖርቱ፡፡
41 አቤቱታ አቅራቢዎች ተገቢው የካሳ ክፍያና በአጠቃላይ ለሁሉም አቤት ባዮች በድምሩ 36ሺ 200 ካ.ሜ ቦታ በምትክነት እንዲሰጣቸውም ተደርጓል፡፡
106 አቤቱታ አቅራቢዎች የጡረታ መብታቸው እንዲከበር እና ያልተከፈለ ውዝፍ ክፍያ 1.4 ሚሊዮን ብር ተከፍሏቸዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው

