top of page

ኢትዮጵያ የአቬሽን ዘርፉ በበረራ ወቅት የሚለቀውን የበካይ ጋዝ መጠን ወደ ዜሮ ለማውረድ የሚያስችላትን ስራ መጀመሯ ተነገረ።

  • sheger1021fm
  • 1 hour ago
  • 2 min read

የህዳር 18 2018


ኢትዮጵያ የአቬሽን ዘርፉ በበረራ ወቅት የሚለቀውን የበካይ ጋዝ መጠን ወደ ዜሮ ለማውረድ የሚያስችላትን ስራ መጀመሯ ተነገረ።


የዚሁ ጉዞ መነሻ ነው የተባለውን ዘላቂ የአቬሽን ዘርፍ የአዋጪነት ጥናት ሰነድን ዛሬ ተረክባለች።


ጥናቱ በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረትና የፈረንሳይ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ በትብብር የተሰራ ነው ተብሏል።


እንደ ጉሎ ፍሬ፣ጎመን ዘር እና ሰናፍጭ ያሉት የግብርና ምርቶች፤ የእንስሳት ሞራ፣ ከየቤቱ የሚወጣ ደረቅ ቆሻሻ ሁሉ በሚፈለገው ልክ ተብላልቶ አካባቢን ከመበከል ነፃ የሆነ የአውሮፕላን ነዳጅን ለማምረት ያስችላል ተብሏል።


የዛፍ ርጋፊ፣ የምግብ ዘይት ተረፈ ምርት ፣ የሸንኮራ አገዳ ያሉት ሁሉ ምርቱን ለመስራት አማራጭ እንደሚሆኑ በጥናት መለየቱ ተነግሯል።


ይህንን ምርት ልክ እንደ ኤታኖል ከመደበኛው የአውሮፕላን ነዳጅ ጋር በመቀላቀል የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን መቀነስ ይቻላል ተብሏል።


በ41ኛው የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ጉባኤ በተወሰነው መሰረት ይህንን መንገድ በመከተል በዓለም ዙሪያ የአቪዬሽን ዘርፍ የሚለቀውን የበካይ ካርበን መጠን በጎርጎሮሳዊያኑ 2050 ወደ ዜሮ ለማስጠጋት ከስምምነት ተደርሷል።

ree

ኢትዮጵያም ከአፍሪካ ቀዳሚ በመሆን ስራውን እየጀመረች ነው ብለዋል የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዶ/ር አለሙ ስሜ፡፡


በጥናቱ እንደተለየው ኢትዮጵያ ይህንን ተኪ የነዳጅ ምርት ለማምረት የሚያስፈልግ በቂ ጥሬ ምርት ያለባት ሀገር መሆኗ ተለይቷል።


እንደ የጉሎ ፍሬ፣ ጎመን ዘር፣ ሰናፍጭ ያለው ምርት በኢትዮጵያ በስፋት እንደሚመረት ያነሱት የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ አበራ እነዚህን ምርቶች ጨምሮ ሌሎች የግብርና እና የእንስሳት ተረፈ ምርቶች ግብዓት መሆን ይችላሉ ብለዋል።


የትኛው መንገድ ለኢትዮጵያ ይሰራል የሚለውን በመለየት ምርቱን ከመደበኛው የአውሮፕላን ነዳጅ ጋር በመቀላቀል መጠቀም ይቻላል ብለዋል።


በዚህ መንገድ እስከ 50 በመቶ ምርቱን ከአውሮፕላን ነዳጅ ጋር መቀላቀል እንደሚቻል ተነግሯል።


የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ቃል በተገባው መሰረት ተግባራዊ የሚደረገው ይህ መንገድ ግን በዋጋ ረገድ ከፍተኛ ወጪን የሚያስወጣና ውድ ነው ተብሏል።


እስከ 50 በመቶ በመቀላቀልም የአቪዬሽን ዘርፍን የበካይ ጋዝ ልቀት በዓለም ዙሪያ እስከ 80 በመቶ መቀነስ ይቻላል ሲባልም ሰምተናል።


በጎርጎሮሳዊው 2008 ቨርጅን አትላንቲክ አየር መንገድ በዚህ መንገድ የመጀመሪያውን በረራ ማድረጉ ይነገራል።


መረጃዎች እንደሚያስረዱት ከጎርጎሮሳዊው 2011 እስከ 2015 ባለው ጊዜ እስከ 50 በመቶ ይህንን አማራጭ ነዳጅ ከመደበኛው ጋር በመቀላቀል በዓለም ዙሪያ ከ2500 በላይ በረራ ተደርጓል።


በአውሮፕላን የነዳጅ አጠቃቀም ላይ ይህንን ለውጥ ማድረግ በሚመረቱት አውሮፕላኖች የሞተር ክፍል ላይ ማሻሻያ ማድረግን ይጠይቅ እንደሆነ ጠይቀን፣ ምንም ማሻሻያ ማድረግ እንደማይጠይቅ ሰምተናል።


ቴዎድሮስ ወርቁ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page