top of page

ነሐሴ 26 2017 - ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ግብይት ለመጀመር በመጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ተነግሯል

  • sheger1021fm
  • 4 hours ago
  • 1 min read

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ግብይት ለመጀመር በመጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ተነግሯል።


ግብይቱን ለመጀመር የታሪፍ የቀረጥ ምጣኔ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወስኖ ሀገራት እንዲያውቁት መደረጉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።


የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ነው።


‘’የዕቃዎች ንግድ ስምምነት’’ የሚባለውና የስምምነቱ የመጀመሪያው ክፍል ሀገራት ከአጠቃላይ ገበያቸው እስከ 90 በመቶ የሚሆነውን በ10 አመት ጊዜ ውስጥ ከታሪፍ ነፃ እንዲያደርጉ ይጠይቃል።


የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ሀገራት ደግሞ ታሪፉን ነፃ የሚያደርጉት በአምስት አመት እንደሚሆን በስምምነቱ ተጠቅሷል።


ሀገራት ከአጠቃላይ ገበያቸው እስከ አስር በመቶ የሚሆነውን ለራሳቸው ምርቶች ብቻ መከለል እንደሚችሉም ተመልክቷል።


ከለላ እየተሰጣቸው ከሚቀጥሉ አስር በመቶ ምርቶች ሶስት በመቶዎቹ በምንም መልኩ ለድርድር የማይቀርቡ እንደሆኑ በስምምነቱ ሰፍሯል።


በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ስምምነቱን መሰረት ያደረገ ግብይት ለመጀመር አብዛኛውን ዝግጅት ጨርሳለች ተብሏል።


ጉሙሩክ ኮሚሽን ለዚሁ የሚያስፈልገውን የአሰራር ስርዓት ሙሉ ለሙሉ ዘርግቶ ይጨርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፤ የዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ንግድ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ታገስ ሙሉጌታ ነግረውናል።


የስምምነቱ አጠቃላይ መንፈስ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ እና ከውጪ የሚገቡ ምርቶች በእኩል አይን እንዲታዩ ማድረግ እንደሆነ አቶ ታገስ ነግረውናል።


ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ከስምምነቱ በፊት የገቢ ዕቃዎች እና ሱር ታክስ ይከፈልባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።


ከውጪም በሚገቡ ፤ በሀገር ውስጥም በሚመረቱ ሸቀጦች ላይ የሚጣሉ የታክስ አይነቶች ግን በዚህ ስምምነት የሚቀሩ አይደሉም ሲሉ አቶ ታገስ ነግረውናል።


እነዚህ ተጨማሪ እሴት ታክስ ፤ ኤክሳይዝ ታክስ እና የትርፍ ግብር ታክስ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።


የአፍሪካ ነጻ የንግድ ስምምነትን 54 የአህጉሩ ሀገራት ፈርመውታል።


ኢትዮጵያን ጨምሮ 47 ሃገራት ደግሞ ከመፈረም አልፈው በየፓርላዎቻቸው አጸድቀውታል።


ኢትዮጵያ ስምምነቱን የፈረመችው በጎርጎርሳውያኑ በ2018 እንደነበር ይታወሳል።


ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን የሚልቀውን የአህጉሪቱ ህዝብ የሚያስተሳስር ግዙፍ ዕድል የሚፈጥር ስምምነት ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ……


ንጋቱ ረጋሳ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page