top of page

ነሀሴ 6 2017 ''መንግስት ከዚህ በኋላ በጥድፊያ የሚጀመሩና በመሠረተ ድንጋይ ደረጃ የሚቀሩ ግንባታዎች እንዲኖሩ አይፈቅድም' ምክትል ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

  • sheger1021fm
  • Aug 12
  • 1 min read

መንግስት ከዚህ በኋላ በጥድፊያ የሚጀመሩና በመሠረተ ድንጋይ ደረጃ የሚቀሩ ግንባታዎች እንዲኖሩ አይፈቅድም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

 

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ማስጀመሪያ መርሃግብር  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ዛሬ በስካይት ላይት ሆቴል ይፋ ሆኗል።

 

በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመስገን ጥሩነህ ዘርፉ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ነው ብለዋል።

 

የግንባታ የጥራት ጉድለት፣ የግብዓት እጥረትና ሙስና  ከችግሮቹ መካከል እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

 

ዛሬ ይፋ የሆነው ኢኒሼቲቭ እነዚህን ችግሮች በማስቀረት ዘርፉን ውጤታማ ያደርጋል የሚል እምነት መንግስት እንዳለውም ተናግረዋል።

 

ቁልፍ የሚባሉ የዘርፉን ተዋናዮች በማሳተፍ የተዘጋጀ ኢኒሼቲቭ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሣኒ ናቸው።

 

ለሚቀጥሉት ሃያ አምስት ዓመታት እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነም ተናግረዋል።

 

ከውጪ የሚገቡ ግብአቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን፣ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምን እንዲሁም በሠው ሃይል ስልጠና፣ ስምሪትና ምዘና ዙሪያ አዳዲስ አሰራሮችን ማስተዋወቅን ታሳቢ ያደረገ ኢኒሼቲቭ ነውም ብለዋል።

 

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ለጥቅል አገራዊ ምርት ወይም #GDP ሃያ በመቶ ድርሻ እንደሚያበረክት ተነግሯል ።

 

አምራች ዜጋ ከሆነው ሃይል ለአስር በመቶው የስራ ዕድል የፈጠረ ነውም ተብሏል።

 

ከ35,000 በላይ ኩባንያዎች ተሠማርተው የሚገኙበት ዘርፍ እንደሆነም በመርሃ ግብሩ ላይ ሲነገር ሠምተናል።

 


ንጋቱ ረጋሳ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page