top of page

ነሀሴ 30 2017 - ከረጃጅም ፅሁፎች ይልቅ አጠር አጠር ወዳሉና ሰዓታት ከሚፈጁ ቃለ መጠይቆች ወይም ንግግሮች ይልቅ በሴኮንድ ግፋ ቢል በደቂቃ እድሜ ወደ ሚያልቁት ማዘንበል

  • sheger1021fm
  • 5 hours ago
  • 1 min read

ከረጃጅም ፅሁፎች ይልቅ አጠር አጠር ወዳሉና ሰዓታት ከሚፈጁ ቃለ መጠይቆች ወይም ንግግሮች ይልቅ በሴኮንድ ግፋ ቢል በደቂቃ እድሜ ወደ ሚያልቁት ማዘንበል በስፋት እየተስተዋለ መሆኑ ይነገራል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ቲክቶክ ዩቲዩብ ያሉ መተግበሪያዎችና የኢንተርኔት መስፋፋት አግዞታል፡፡


ሰዎች ረጃጅም ምስሎችን ከማየት፣ረዘም ያሉ ንግግሮችን ከመስማት፣ብዙ ገፅ የያዙ መፅሐፍትን ከማገላበጥ ርቀው የዘመኑ ቴክኖሎጂ ወደ አመጣው ጊዜ ቆጣቢና አጫጭር ነገሮች ላይ ማተኮራቸው ጥቅሙ እንዳለ ሆኖ ጉዳቱም ግን በዚያው ልክ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡


በቅርቡ በተደረገ ጥናት ሰዎች አጫጭር ቪዲዮዎችን አብዝተው በማየታቸው ብቻ አዕምሮአቸው አንድ ነገር ላይ ትኩረት የማድረግ አቅሙን ወደ 47 ሰከንድ በማውረድ ትዕግስት የለሽ እና ችኩል ትውልድ እየፈጠረ ነው ተብሏል፡፡


አቶ ቴዎድሮስ ጌትዬ የሰዎች ስነ ባህሪ ጥናት ባለሞያ ናቸው፡፡ ባለሞያው ሰዎች በአጭር ቪድዮ የስነ ልቦና ተፅዕኖ ስር መግባታቸው፣ ኑሮአቸው ላይም ትኩረታቸውን በስራ ሂደት ላይ ሳይሆን በመጨረሻው ውጤት ላይ ብቻ በማድረግ ለለውጥ ሁሌም አቋራጭ መንገድን እንዲመርጡ ስነ ልቦናዊ ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል ይላሉ፡፡

የሰዎች ስነ ባህሪ ጥናት ባለሞያው አጫጭር ቪድዮዎችን ያለ ገደብ ማየት ለነገሮች ትኩረት የመስጠት እና የማስተዋል ችሎታን ይቀንሳል፣ ረጅም ፅሁፍ ማንበብ፣ በእርጋታ የሚከናወኑ ተግባራትን ለመከወን መሰላቸትን ያስከትላል ያሉን ሲሆን ዝርዝሮችን በቀላሉ ለማስታወስ መቸገር ያመጣል። የእንቅልፍ እና የዕረፍት ጊዜን ያዛባል ብለዉናል።

በቅርቡ በተደረገ ጥናት በአጫጭር ቪድዎች ሱስ መጠመድ የአልኮል ሱስ በአእምሮ ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት ጋር ተመሳሳይ ነው ተብሏል፡፡


ይህንን ጉዳት ለመቀነስ ዕለታዊ የስክሪን ጊዜ ገደብን መወሰን፣ ጤናማ እና ትምህርታዊ የሆኑ ይዘቶችን መምረጥ፣ ስፖርት መስራት፣ መፅሃፍ ማንበብ፣ ከተፈጥሮ ጋር ጊዜ ማሳለፍ፣ ከወዳጆች ጋር መጨዋወት የመሳሰሉ ልምምዶችን ማዘውተር፣ ጤናማ የሆኑ የዲጂታል ልምምዶችን መከተል እንደሚያስፈልግ ባለሙያው መክረዋል።



ንጋት መኮንን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page