ነሀሴ 17 2017 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Aug 23
- 2 min read
በምዕራብ አፍሪካዊቱ ሀገር ጋምቢያ በሰዎች ላይ ቁም ስቅል እና ማሰቃየት አድርሷል የተባለ የቀድሞ የጦር ባልደረባ አሜሪካ ውስጥ የ67 ዓመታት እስር ተፈረደበት፡፡
ግለሰቡ በጋምቢያ በለየላቸው አምባገነንነታቸው ይታወቁ በነበሩት በቀድሞው መሪ ያህያ ጃሜ ተቋቁሞ የነበረ ገዳይ እና አሰቃይ ቡድን አባል ነበር ተብሏል፡፡
ቡድኑ ጃሜህ በተቃዋሚነት በሚጠረጥሯቸው ሰዎች ላይ ሳይቀር እስከ ሕይወት ማሳጣት የደረሰ ማሰቃየት ይፈፅም ነበር ይባላል፡፡

የዚህ አሰቃይ ቡድን ባልደረባ ነበር በተባለው ግለሰብ ላይ ከ67 ዓመታት በላይ እስር የፈረደው የኮሎራዶ ፍርድ ቤት እንደሆነ ሬውተርስ ፅፏል፡፡
ጃሜህ ከ8 ዓመታት ገደማ በፊት በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ቢያንገራግሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ወደ በስደተት ኑሯቸውን በጊኒ ቢሳዎ ማድረጋቸው ይነገራል፡፡
በቅድሚያ በወታደራዊ የመንግስት ግልበጣ ፕሬዘዳንት የነበሩት ያህል ጃሜ አገሪቱን ለ22 አመታት መምራታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጋዛ እየተባባሰ የመጣው ረሃብ የሰብአዊነት ውድቀት ነው አሉ፡፡
በምህፃሩ IPC የተሰኘው የድርጅቱ አካል በጋዛ እና በአቅራቢያዋ ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ለከፋ ረሃብ ተጋልጠዋል ማለቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የጋዛው ረሃብ ሰው ሰራሽ ነው ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
እስራኤል ወደ ጋዛ ሰርጥ የሚገባውን ሰብአዊ እርዳታ እያገደች እና እያከላከለች መሆኑ ይነገራል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ መንግስት ግን በጋዛ ረሃብ ግብቷል መባሉን ያስተባብላል፡፡
በIPC የወጣው ሪፖርት ግን በጋዛ ከእለት እለት ረሃቡ እየከፋ እና አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን ያሳያል ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የእስራኤል መንግስት በጋዛ ረሃብ የለም ማለቱ ከ100 በላይ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶችን ተጨባጭ ምስክርነት የሚቃረን ነው ማለቱን መረጃው አስታውሷል፡፡
የኒጀር ጦር የቦኮ ሐራሙን ፅንፈኛ ቡድን መሪ ኢብራሂም ባኩራን ገደልኩት አለ፡፡
የኒጀር ጦር የፅንፈኛው ቡድን መሪ በቅርቡ ባካሄድኩት የአየር ድብደባ ተገሏል ማለቱን ሌጀት ድረ ገፅ ፅፏል፡፡
ተገደለ የተባለው የፅንፈኛው ቡድን መሪ በሕይወት አለሁ አልተገደልኩም ማለቱ በዘወርዋራ ተሰምቷል፡፡
ይህም የሰውየውን መጨረሻ አሻሚ አድርጎታል ተብሏል፡፡
ቦኮሐራም መነሻው ከናይጀሪያ ቢሆንም እንደ ኒጀር ያሉ ጎረቤት አገሮችንም በሽብር ጥቃቶች በማመስ ገፍቶበታል፡፡
ፅንፈኛው ቡድን አካባቢውን በሽብር መናጥ ከጀመረ ከ16 አመታት በላይ እንደሆነው መረጃው አስታውሷል፡፡
#የኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የቆዩት ካስፓር ቬልድ ካምፕ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ፡፡
ቬልድ ካምፕ ሃላፊነታቸውን የለቀቁት በእስራኤል ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች እንዲጣሉባት ያቀረቡት ሀሳብ በካቢኔው አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘቱ ምክንያት ነው መባሉን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ካስፓር ቬልድ ካምፕ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በምታካሂደው ዘመቻ በሰላማዊ ፍልስጤማውያን ላይ እልቂት እያደረሰች ነው በሚል በፅኑ ከሚቃወሙት መካከል ናቸው ይባላል፡፡
በዌስት ባንክም አይሁዳውያን ሰፋሪዎች በግዛቲቱ ፍልስጤማውያን ላይ ያደርሱታል የሚባለው ግድያ ፣ ዘረፋ እና ቁም ስቅል ነቃፊ እንደሆኑ ይነገራል፡፡
እስራኤል የጋዛ ዘመቻዬ የህልውና ዘመቻ ነው ስትል ቆይታለች፡፡
የኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀላፊነታቸው የለቀቁ ሲሆን በማን እንደሚተኩ ገና የታወቀ ነገር የለም፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments