ነሀሴ 15 2017 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 5 hours ago
- 2 min read
ምስራቅ አፍሪካዊቱ ዩጋንዳ ከአሜሪካ ተባራሪ ስደተኞችን ለመቀበል በጭራሽ አልተስማማሁም አለች፡፡
ቀደም ሲል CBS ዩጋንዳ ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል መስማማቷን የሚያሳይ ሰነድ አግኝቻለሁ በማለት ዘግቦ እንደነበር አናዶሉ አስታውሷል፡፡
ዘገባው ዩጋንዳ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ እስያውያን ስደተኞችን ለመቀበል መሰናዳቷን የሚጠቁም ነበር፡፡
ይሁንና የዩጋንዳው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኦኬሎ ኦሪም ከአሜሪካ ተባራሪ ስደተኞችን ለመቀበል በጭራሽ አልተስማማንም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
እስካሁን ከአፍሪካ አገሮች መካከል ደቡብ ሱዳን እና ኢስዋቲኒ የተወሰኑ ከአሜሪካ ተባራሪ ስደተኞችን የተቀበሉ አገሮች ናቸው፡፡
ሩዋንዳም ከአሜሪካ ተባራሪዎቹ ለመቀበል የተስማማች አገር እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
በኖርዌይ ለሩሲያ እና ለኢራን ሲሰልል ተደርሶበታል የተባለ ወጣት የአገሪቱ ዜጋ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ነው ተባለ፡፡
በስለላ ተጠርጥሮ ጉዳዩ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የሚገኘው ኖርዌያዊ ወጣት በአገሪቱ የአሜሪካ ኤምባሲ የጥበቃ ባልደረባ ነበር መባሉን የፃፈው AFP ነው፡፡
ግለሰቡ ለውጭ ቀጣሪዎቹ የኤምባሲውን ዲፕሎማቶች አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና የግንኙነት መስመር የተመለከቱ መረጃዎችን ሲያቀብል ነበር ተብሏል፡፡
የኤምባሲውን ህንፃ ንድፍም የተመለከቱ መረጃዎችን ማስተላለፉ ተጠቅሷል፡፡
የፍርድ ሒደቱ ተፋጥኖ እንደሚቋጭ ታውቋል፡፡
ጥፋተኝነቱ በፍርድ ቤት ከተረጋገጠበት እስከ 21 ዓመታት የእስር ቅጣት እንደሚከናነብ መረጃው አስታውሷል፡፡
ግብፅ የፍልስጤማውያኑን ታጣቂ ቡድን የሐማስን የጦር መሳሪያዎች ተቀብላ በአደራ ለማስቀመጥ ሀሳብ አቅርባለች መባሉን በስም ያልተጠቀሱ ከፍተኛ ባለስልጣን ሐሰት ነው ሲሉ ማስተባበላቸው ተሰማ፡፡
ግብፅ የሐማስን የጦር መሳሪያዎች በአደራ ለማስቀመጥ ሀሳብ አቅርባለች መባሉን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ብዙ እንደፃፉበት እና እንዳወሩበት ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
ካይሮ ኒውስ እንደዘገበው በስም ያልተጠቀሱት የግብፅ ከፍተኛ ሹም የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘገባ በጭራሽ ሐሰት ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ግብፅ በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረስ የተባባሪ አደራዳሪነት ሚና እየተጫወተች ነው፡፡
ሌላኛዋ ሸምጋይ አገር የባህረ ሰላጤዋ ካታር እንደሆነች ይታወቃል፡፡
አዲሱን የተኩስ አቁም ሐሳብ ሐማስ ተቀብየዋለሁ ቢልም እስራኤል እያመነታች መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡
አሜሪካ በተጨማሪ 4 የአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት /ICC/ ባልደረቦች ላይ ማዕቀብ ጣለችባቸው፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ሁለት ዳኞች እና ሁለት አቃቢያነ ህግ ላይ ማዕቀብ እንደተጣለባቸው እወቁልን ማለታቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ችሎቱ ቀደም ሲል በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና በቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአብ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡
አሜሪካ በችሎቱ ባልደረቦች ላይ ማዕቀቧን እያከታተለች የምትገኘው በዋናነት በዚሁ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
ማርኮ ሩቢዮ ICC የአሜሪካም ሆነ የእስራኤል የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው ብለውታል፡፡
ችሎቱ ቀደም ሲል በእስራኤላውያን ባለስልጣናት ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ያወጣባቸው በጋዛ ዘመቻቸው ተፈፅሟል ባለው የጦር ወንጀል ምክንያት እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሜሪካ በችሎቱ ባልደረቦች ላይ ማእቀብ መጣሏን አምርሮ ኮንኖታል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments