top of page

ነሀሴ 1 2017 - በኢትዮጵያ በካንሰር ምክንያት ከሚከሰተው ሞት 1.5 በመቶ የሚሆነው በሳምባ ካንሰር የሚመጣ ነው ተባለ

  • sheger1021fm
  • Aug 7
  • 2 min read

በኢትዮጵያ በካንሰር ምክንያት ከሚከሰተው ሞት 1.5 በመቶ የሚሆነው በሳምባ ካንሰር የሚመጣ ነው ተባለ፣ ነገር ግን ቁጥሩ በታወቁ የህክምና ተቋማት የተመዘገበ እንጂ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ተነግሯል፡፡


በሀገሪቱ በዓመት ከ80,000 በላይ ሰዎች በተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች ህይወታቸውን ያጣሉ ተብሏል፡፡


ቅድመ መከላከል በተለይም ምርመራና ህመሙ ሳይባባስ መለየቱ ላይ በብርቱ ስላልተሰራበትም በኢትዮጵያ በካንሰር ምክንያት የሚመዘገበው የሞት መጠን እየጨመረ መምጣቱን ጥናት አሳይቷል፡፡


የሳምባ ካንሰርን በተመለከተ ያለውን ሀገራዊ መጠን ለማወቅ የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ የተለያዩ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ተናግሯል፡፡


በዓለም አቀፍ ደረጃ ከካንሰር ዓይነቶች ከፍተኛ ቁጥር የሚይዘው የሳንባ ካንሰር በኢትዮጵያም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱንና የሚመዘገቡ የሞት መጠኖችም እየጨመሩ መሆኑን የሚናገሩት በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአእምሮ ጤና ዴስክ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሰላማዊት አየለ ናቸው፡፡

ree

በዓመት ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች በካንሰር ህመም ይሞታሉ የሚሉት ዶ/ር ሰላማዊት በአለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው በጣም ገዳይ የሆነው የሳምባ ካንሰር ነው፤ በኢትዮጵያ በቂ ጥናቶች ባይኖሩም ከህክምና ተቋማት የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ወደ አንድ ነጥብ አምስት በመቶ የሚሆነው የካንሰር ሞት የሚከሰተው በሳምባ ካንሰር ነው ብለዋል፡፡


በኢትዮጵያ የሳምባ ካንሰር ስርጭት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ እንዲሁም በዘርፉ የሚደረጉ የመከላከልና ህክምና ስራዎችን ለማገዝ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ እየሰሩ መሆኑን የነገሩን ደግሞ የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት እና የህፃናት የሳምባና የጽኑ ህሙማን ሰብ ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶክተር ራሄል አርጋው ናቸው፡፡


በምርምር ኢትዮጵያ ያለችበት የካንሰር ደረጃ ምንድነው? ተጋላጭነቱስ? ታካሚዎች ምን ደረጃ ላይ ሆነው ነው የሚመጡት? በቂ ህክምና ያገኛሉ ወይም ያላገኙበት ምክንያቶች ምንድናቸው? የሚለውን መረጃዎችን በመሰነድ ለሚደረጉ የህክምና ሂደቶች እንዲያግዙ እየሰራን ብለዋል፡፡


ካንሰርን ሳይሰራጭ በጊዜ ለማወቅ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ዋናው መፍትሄ መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር ራሄል አሁን ላይ በተለይ ህመሙ በብዛት እየታየ ያለው ለተበከለ አየር በመጋለጥ በመሆኑ ቅድመ ምርመራ ላይ በስፋት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡


የካንሰር ህክምና በተለይም በሳንባ ካንሰር ምርመራና ህክምና ላይ ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎችም አለም አቀፍ ለጋሾች ጋር በመሆን ካንሰርን ሳይባባስ በማከም የተሻሉ ውጤቶች እንዲኖሩ ለማድረግ ፕሮጀክቶች ቀርጸን እየሰራን ነው የሚሉት ደግሞ የማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ወንዱ በቀለ ናቸው፡፡


በኢትዮጵያ ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆኑት የሳምባ ካንሰር ታካሚዎች ህመሙ ከተባባሰ በኋላ ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ በመሆኑ ህክምናው ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል ተብሏል፡፡


ለዚህም የካንሰር ደረጃው ስር ሳይሰድ በቅድመ ምርመራ መለየት እንዲሁም አጋላጭ ከሆኑ እንደትምባሆ ማጨስና ለረጅም ጊዜ ለተበከ ፤ አየር መጋለጥ ያሉ ችግሮችን ማስቀረት ያስፈልጋል መባሉን ሰምተናል፡፡


ምህረት ስዩም


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments

Couldn’t Load Comments
It looks like there was a technical problem. Try reconnecting or refreshing the page.
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page