በየጊዜው የሚለዋወጡ ህጎች የኢንቨስትመንት መስኩ ተገማች እንዳይሆን ማድረጉን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተናገረ።
- sheger1021fm
- 46 minutes ago
- 2 min read
ህዳር 12 2018
በየጊዜው የሚለዋወጡ ህጎች የኢንቨስትመንት መስኩ ተገማች እንዳይሆን ማድረጉን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተናገረ።
የፀጥታ ችግርም እንቅፋት እንደሆነበት ኮሚሽኑ ለህዝብ እንደራሴዎች ተናግሯል፡፡
ኪሚሽኑ ይህን የተናገረው የሶስት ወራት የስራ ክንውን ሪፖርቱን በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትናንት ህዳር 11 ቀን 2018 ዓ.ም ባቀረበበት ወቅት ነው።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽንን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሪፖርት በንባብ ያቀረቡት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዳገቶ ኩምቢ ባለፉት 3 ወራት 400 ሚሊዮን ዶላር በተኪ ምርት ወይንም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ታቅዶ መፈጸም የተቻለው ግን 211 ሚሊዮን ዶላር ወይንም የእቅዱን 53 በመቶ እንደሆነ አስረድተዋል።
19 የሚሆኑ ድርጅቶች ከህግ ወጭ የሆነ ስራ በመስራታቸው ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ ከዚህ ውስጥ ለ10 የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ፣ 3 ድርጅቶች ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ ተድርጓል ፣ እንዲሁም 5 ድርጅቶች አላግባብ የተጠቀሙትን የታክስ መብት እንዲከፍሉ ተደርጓል ተብሏል ።
123 የውጭ አገር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ለማልማት የኢንቨስትመንት ፍቃድ በ3 ወራት መውሰዳቸውንም ኮሚሽኑ ተናግሯል።
በዚህም በአምራች ዘርፍ ለመሰማራት የተወሰደው ፍቃድ ቀዳሚ ነው የተባለ ሲሆን በቅርቡ ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን የወሰነችው ገቢ እና ወጪ ንግድ ደግሞ 34 ባለሀብቶች ፍቃድ መውሰዳቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ከአገልግሎት ክፍያ 27 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 36 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ምክትል ኮሚሽነር ዳገቶ ኩምቢ ተናግረዋል።
ይህም ባለፈው ዓመት ከተሰበሰበው የዘንድሮው የሩብ ዓመት በብዙ እጥፍ ይበልጣል ተብሏል።
አቶ ዳገቶ በሩብ አመቱ ያጋጠሙ ችግሮችን ሲዘረዝሩ የአንደኛው "ኢ ተገማች" ሁኔታ ነው ብለዋል።
"ህጎች በሚወጡበት ጊዜ ፣ አሰራሮች በሚቀየሩበት ሁኔታ ለባለሀብቶች በጊዜ አለማሳወቅ" መኖሩን ተናግረዋል።
ባለሀብቶች ስራ ላይ አለ ብለው የሚወስኗቸው ህጎች ድንገት ይቀየራሉ ይሄ እንደ ችግር በተደጋጋሚ የሚቀርብ ቅሬታ ነው ሲሉ ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ አንድ አንድ አካባቢዎች ያሉ የጸጥታ ችግሮች የአለም አቀፍ ሁኔታም እንቅፋት እንደሆኑበት ተቋሙ ጠቁሟል።
እነዚህን ችግሮች በተለይ ደግሞ ተገማች ያልሆኑ የህግ እና አሰራር ሁኔታዎችን ለመፍታት ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር ፣ ከጉሙሩክ ኮሚሽን እና ጉዳይ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ውይይት መካሄዷን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አስረድተዋል።
በዚህም ኢንቨስትመንትን የተመለከቱ ህጎች ሲወጡ ከሚሽኑን ያካተተ እንዲሆን ተሰርቷል ብለዋል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….
ያሬድ እንዳሻው ያዘጋጀውን በምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








