በዓመት በአማካይ እስከ 2,000 ጉዳዮች የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያገኙ ለፌዴሬሽን ም/ቤት እየላከ መሆኑን፤ የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ተናገረ፡፡
- sheger1021fm
- 32 minutes ago
- 1 min read
ህዳር 22 2018
በዓመት በአማካይ ከ1,500 እስከ 2,000 ጉዳዮች የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያገኙ ለፌዴሬሽን ም/ቤት እየላከ መሆኑን የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ተናገረ፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ስለሚሰበሰብ የሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ እንዲዘገይ አድርጎታል ሲልም ጉባኤው ነግሮናል፡፡
ጉባኤው ህገ-መንግስታዊ ትርጓሜን የሚሹ አቤቱታዎችን ተቀብሎ በመመርመር የተለያዩ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል፡፡
ውሳኔው የመጨረሻ ባለመሆኑ ውሳኔውን በምክረ ሃሳብ መልክ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል፤ምክር ቤቱም ጉዳዩን ተመልክቶ የመጨረሻውን ውሳኔ ይሰጣል ሲል ጉባኤው ነግሮናል፡፡

አቶ ደበበ ሃይለገብርኤል የህግ ባለሙያና የጉባኤው አባል ናቸው፤ጉባኤው እነዚህን ስራዎች ሲከውን ቆይቷል በዓመትም በአማካኝ ከ1500 እስከ 2000 ጉዳዮችን ተመልክቶ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ወደ ምክር ቤቱ ይመራል ብለውናል፡፡
ይሁንና የፌደሬሽን ምክር ቤትን የመጨረሻ ውሳኔ የሚፈልጉ ይህን ያህል ጉዳዮች ቢኖሩም ምክር ቤቱ በዓመት 2 ጊዜ ብቻ የሚሰበሰብ መሆኑና ብዙ ጊዜ የማይቀመጥ መሆኑ ለሚቀርቡ ጉዳዮች የሚሰጠው ውሳኔ እንዲዘገይ ምክንያት ሆኗል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ያለፈው 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ የሚለውን ለመወሰን ህገ መንግስታዊ ትርጉም የተሰጠበት ጉዳይ ላይ የባለሙያዎች ስብስብ የሆነው ጉባኤው ድርሻ እንደነበረውም ያስታውሳሉ፡፡

ሌላኛው የጉባኤው አባል አቶ ምትኩ ማዳ፤ በትግራይ ክልል ከህገ መንግስቱ የሚቃረኑ ህጎች ወጥተዋል የሚሉ አቤቱታዎች፤ የቤት ኪራይን በተመለከተ በፌድራል መንግስተቱና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የወጡ መመሪያዎች ህገመንግስታዊ መብትን የሚጥሱ ናቸው የሚሉ አቤቱታዎችም ቀርበውና የጉባኤውን ውሳኔ አግኝተው ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የተመሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..
ምንታምር
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp https://tinyurl.com/ycxjmm3s








