top of page

በኮምቦልቻ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ከፍተኛ ሕመም ያጋጠማቸው ታራሚዎች ወደ አዲስ አበባ ሄደው ሕክምና እንዲያገኙ ኢሰመኮ አሳሰበ።

  • sheger1021fm
  • 11 hours ago
  • 2 min read

ጥር 17/2018


በኮምቦልቻ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ከፍተኛ ሕመም ያጋጠማቸው ታራሚዎች ወደ አዲስ አበባ ሄደው ሕክምና እንዲያገኙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) አሳሰበ።


ኮሚሽኑ ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው በአማራ በክልሉ በሚገኙ 5 ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ወይይት ማካሄድን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት ነው።


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን አስመልክቶ በ2017 ዓ.ም የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ለማወቅ  ታኅሣሥ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ወይይት ማድረጉን ተናግሯል።


በወይይቱ፤ በማረሚያ ቤቶች የመጠጥ እና ንጽሕና መጠበቂያ ውሃ አቅርቦት ችግር መፈታቱ፣ ለታራሚዎች ግልጽ የቅሬታ ማቅረቢያ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱ፣ ሴት ታራሚዎች በገቢ ማስገኛ፣ በትምህርት እና ልዩ ልዩ ሙያዎች ሥልጠና ላይ ያላቸው ተሳትፎ መሻሻሉ፣ ለሴት ታራሚዎች የግል ንጽሕና መጠበቂያ ከግል ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመሥራት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑ እና መሰል ሁኔታዎች መሻሻላቸው ተመልክቻለሁ ብሏል ኢሰመኮ።


የኮምቦልቻ ማረሚያ ቤት ቅጥር ግቢ መጥበብ ለታራሚዎች መጨናነቅ ምክንያት መሆኑ፣ ከፍተኛ ሕመም ያጋጠማቸው ታራሚዎች ወደ አዲስ አበባ ሄደው ሕክምና ማግኘት አለመቻላቸው፣ ለአንድ ታራሚ የተመደበው የቀን የምግብ በጀት በቀን ብር 55 አሁን ላይ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር በቂ አለመሆኑ እና በሐኪም የሚታዘዝ ልዩ ምግብ ከበጀት ጋር በማያያዝ አለመፈጸም ያልተፈቱ ችግሮች በመሆናቸው እንዲፈቱ ጠይቋል።


በተጨማሪም ታራሚዎች ከማረሚያ ቤት ውጭ ላላቸው ጉዳይ የጉዳይ አስፈጻሚ ባለሙያ አገልግሎት አለማግኘታቸው፣  የስፖርት ማዘውተሪያና ካፍቴሪያ ያሉ የጋራ መገልገያዎች የውስጥ ገቢን ለማሳደግ በከፍተኛ ዋጋ ለነጋዴዎች በጨረታ መሰጠታቸው ታራሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እንዳያገኙ ስላደረገ እንዲፈቱ ኢሰመኮ አሰስቧል።


የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤን የሕግ፣  የክልሉ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሰላምና ጽጥታ ቢሮ፣ ፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እና ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ተወካዮች እንዲሁም ክትትሉ የተደረገባቸው 5 ማረሚያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ወይይቱ መካሄዳን ተቋሙ አስረድቷል ።


የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ ኢሰመኮ በክትትሉ በዝርዝር የለያቸውን ግኝቶች እና የሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦች በበጎ እንደሚቀበሉትና የክልሉ ምክር ቤት በሚያከናውናቸው የክትትል ሥራዎች ሪፖርቱ በግብዓትነት እንደሚወስድ በመደረኩ ላይ ተናግረዋል።


የኢሰመኮ ባሕር ዳር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ  አማረ ተስፋዬ (ዶ/ር) ኢሰመኮ የታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን ማሻሻል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page