በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ከዓመታት በፊት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስሳትን ከገደለው ድርቅ እስካሁን ያላገገሙ አሉ ተባለ፡፡
- sheger1021fm
- Nov 26
- 2 min read
ህዳር 17 2018
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ከዓመታት በፊት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስሳትን ከገደለው ድርቅ እስካሁን ያላገገሙ አሉ ተባለ፡፡
ድርቁ አፈናቅሏቸው ከመጠለያ ጣቢያ መውጣት ያልቻሉ እንዳሉ ሰምተናል፡፡
በድርቁ የተጎዱት አርብቶ አደሮች እንደመሆናቸው የሞቱባቸውን እንስሳት መልሰው መተካት አልቻሉም ተብሏል፡፡
ከአራት ዓመት በፊት በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ በአብዛኛው አርብቶ አደር በሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከበድ ያለ ጫና አሳድሮ አልፏል።
ድርቁ በሚሊየን የሚቆጠሩ እና የአርብቶ አደሩ የህይወት መሰረት ናቸው የሚባሉ የቤት እንስሳት እንዲሞቱ ምክንያት የሆነ ነው።
ብዙዎችም አካባቢያቸውን ጥለው ወደ ሌላ ስፍራ እንዲሄዱ ማስገደዱ ተነግሯል።
ዛሬ ላይ ብዙዎች ከዚህ ተፅዕኖ ተላቀዋል ቢባልም አሁንም ማገገም ያልቻሉ ሰዎች እንዳሉም ተሠምቷል።
በተለይ በዞኑ ዱቡሉቅ ተብሎ በሚጠራው የወረዳ ከተማ ተጠልለው ያሉ አርብቶ አደሮች አሁንም ችግር ላይ ናቸው ተብሏል።
አርብቶ አደሮቹ የሞቱባቸውን የቤት እንስሳት እስከ አሁን መተካት እንደ ከበዳቸው እና ፤ ወደ ቀዬቻውም መመለስ እንዳልቻሉ ተጠቅሷል።
ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የዱቡሉቅ ወረዳ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ እስማኤል ኢዶ በከተማዋ አቅራቢያ ተጠልለው ከነበሩ አስር ሺህ ገደማ ሰዎች አራት ሺህ ያህሉ አሁንም እንዳልተመለሱ ነግረውናል።
መልሰው እንዲቋቋሙ ከፍተኛ ጥረት ያደረግን ቢሆንም ሁሉንም ወደ ቀዬቻው መመለስ አልቻልንም ነው ያሉት።
በመጠለያ ጣቢያው ያሉ ሰዎች ከደርቁ ተፅዕኖ እንዲላቀቁ አሁንም እየሰራን ነው ያሉት አቶ እስማኤል የሞቱባቸው የቤት እንስሳት እንዲተኩላቸው ማድረግ አንዱ መሆኑን ነግረውናል።
እዚያው በከተማው አካባቢ መቆየት የሚፈልጉትን ደግሞ በጥቃቅን እና አነስተኛ ስራዎች ለማሰማራት ስልጠና እየሰጠን ነው ብለውናል።
የኦሮሚያ ክልል መስኖ እና አርብቶ አደር ቢሮ በበኩሉ መሰል ድርቅ ቢከሰት እንደቀደመው አይነት ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል እና የቀደሙትን የማቋቋም ስራዎች አንድ ላይ ሲሰሩ እንደቆዩ አስታውሷል።
የመስኖ ልማት በአካባቢው እንዲለመድ እና አርብቶ አደሮች ለቤት እንስሳቶቻቸው የመድን ሽፋን እንዲኖራቸው የተጀመረው ስራ መሰል ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል እየተከወኑ ያሉ ተግባራት ናቸው ብሏል።
የቀደሙትን ማቋቋሙ ደግሞ ህብረተሰቡን በማስተባበር ጭምር ሲሰራ የቆየ እንደሆነ የቢሮው ምክትል ሃላፊ ሃላፊ አቶ ሮባ ቱርጬ ነግረውናል።
አርብቶ አደሮች መስኖ በመጠቀም ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች የእርሻ ልማት እንዲያከናውኑ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ምክትል ቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል።
ክልሉ ከሁለት ዓመት በፊት በተለያየ ጊዜ በሚከሰት ድርቅ የቤት እንስሳቶቻውን የሚያጡ አርብቶ አደሮችን ከጉዳት ለመጠበቅ የእንስሳት መድን ሽፋን መጀመሩንም አስታውሷል።
የኑሮ መሰረቱን በቤት እንስሳት ላይ ያደረገው አርብቶ አደር በድርቅ ወቅት እንዳይጎዳ የመድን ሽፋን ይኑረው የሚለው ሃሳብ ፤ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (IGAD) እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s











Comments