በኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብን፣ የአየር ንብረት ለውጥንና ሥርዓተ ጾታን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሥራዎች አንዱ ከአንዱ ጋር ተናበው የሚከወኑ ባለመሆናቸው ውጤት ከማምጣት ይልቅ ችግሩን ውሃ ቅዳ፣ ውሃ መልስ አድርጎታል ተባለ።
- 3 hours ago
- 2 min read
ነሐሴ 14 2018
በኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብን፣ የአየር ንብረት ለውጥንና ሥርዓተ ጾታን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሥራዎች አንዱ ከአንዱ ጋር ተናበው የሚከወኑ ባለመሆናቸው ውጤት ከማምጣት ይልቅ ችግሩን ውሃ ቅዳ፣ ውሃ መልስ አድርጎታል ተባለ።
ሥርዓተ ምግብና የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱት ችግሮች ተጽዕኗቸው በቀጥታ ተጎጂ የሚያደርገው ሴቶችን በመሆናቸው በእነዚህ ላይ ሲሰራ የሥርዓተ ጾታ ጉዳይን ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ተነግሯል።
በኢትዮጵያ በዚህ ላይ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ የቆየው 'ጂካን' የተባለ ፕሮጀክት ይህንን ለማስቀረት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር የተለያዩ ጥናቶች በማድረግና የመፍትሔ ሀሳቦች የተካተቱበት ምክክርና ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሷል።
ዶክተር ሰላም ኢሳያስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ የትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም የፕሮጀክቱ መሪ ናቸው እርሳቸው እንደሚሉት ፕሮጀክቱ አላማው ዋናው በኢትዮጵያ ምግብ ፣ በግብርና ፣ እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚቀረጹ ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች እነዚህን ሶስት ጉዳዮች አንድ ላይ አቀናጅቶ ከማስራት አኳያ የተሻለ ልምድ እንዲኖር የሚያግዝ ወይም ያንን አላማ አድርጎ ይዞ የተነሳ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ተከትለው የሚመጡት እንደ ሥርዓተ ምግብ ያሉ ችግሮች በቀጥታ ዳፋቸው የሚያርፈው ሴቶች ላይ መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር ሰላም፣ ኢትዮጵያ ላይ ይህንን ለማስቀረት የሚሰሩት አብዛኞቹ ፕሮጀክቶችና የመፍትሔ ሀሳቦች ግን የተነጣጠሉና አንድ ላይ የሚከወኑ ባለመሆናቸው ውጤታቸውን ማየት አልቻልንም ይላሉ።
ፕሮጀክቱን በጋራ ከሚከውኑት ተቋማት አንዱ የሆነው 'ውመን ኢንፓወርመንት አክሽን' በተባለ ተቋም የፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ለማ ተስፋዬ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ከብዙ ጉዳዮች ጋር እንደሚያያዝና በተለይም ችግሩ ሴቶችን ተጎጂ ስለሚያደርግ በየጊዜውም ወቅት እየጠበቀ የሚከሰት በመሆኑ መፍትሔው ላይ በቋሚነት መሰራት አለበት ይላሉ።
አብዛኞቹ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለማምጣት የሚሰሩ ሥራዎች ምንም እንኳን የአንዱ ችግር መነሻው ከሌላው ጋር የሚያያዝ ቢሆንም ከየአየር ንብረት ለውጥና ከሥርዓተ ምግብ እንዲሁም ከሥርዓተ ጾታ ጋር የተገናኘው አንዱ መሆኑን የሚጠቅሱት በ MSI ኢትዮጵያ የጥናት አማካሪና የሥርዓተ ምግብ ጉዳይ ተወካይ የሆኑት ዶክተር ማቲያስ አጠናፉ ናቸው።
"ብዙ ፕሮግራሞቻችን አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ናቸው የሚሉት ዶክተር ማቲያስ አንዱ ላይ ላይ ስንስራ አንዱን እንረሳዋለን፤ በዚህም ምክንያት ሰርተን ሰርተን ስንጨርስ የመጣውን ውጤት መለካት አንችልም ብለዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም በተከወነው የዳሰሳ ጥናት ምንም እንኳን አንዱ ከአንዱ ተነጣጥሎ ውጤት ባያመጣም ሥርዓተ ምግብና የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ሥርዓተ ጾታን የተመለከቱ ጉዳዮች በተናጠል ሲሰራባቸው መቆየቱን አሳይቷል ተብሏል።
ለዚህም አሁን በፕሮጀክቱ ከሚተገበሩ ሥራዎች መካከል የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ሶስቱን ያሰተሳሰረ እንዲሆን ለማድረግ ከመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች ጋር በጋራ እንደሚሰራበት ሰምተናል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ.....
ምህረት ስዩም
_edited.jpg)



Comments