''በተመደቡበት መስመር ላይ ረዥም ደቂቃ የሚቆሙ አሽከርካሪዎች የመቆጣጠሪያ ዘመናዊ መላ በመጠቀም ክትትል እያደረግሁ ነው'' የአዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት
- sheger1021fm
- 2 hours ago
- 1 min read
ታህሳስ 10/2018
የአዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት በተመደቡበት መስመር ላይ ረዥም ደቂቃ የሚቆሙ አሽከርካሪዎችና የተመደቡበትን መስመር በአግባቡ ስለመሸፈናቸው ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ መላ በመጠቀም ክትትል እያደረግሁ ነው አለ።
ድርጅቱ የአገልግሎት ታሪፍ ጭማሪ አድርጓል የሚል ቅሬታ ቢቀርብም የከተማ አውቶብስ ተጠቃሚዎች አንዳንዴ የተራዘመ መስመር ሲጠቀሙ ከተቀመጠው ታሪፍ በተጨማሪ ይከፍላሉ እንጂ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ አይደለም ብሏል።
የአዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት አዳዲስ በተመሠረቱ የመኖሪያ አካባቢዎች ላይ የሚያጋጥም የትራንስፖርት እጥረት ለማስተካከል የመጠበቂያ ሰዓቱን በማሳጠር የትራንስፖርት አገልግሎቱ እንዲደረስ ለማድረግ ጥረት እያደረግሁ ነው ብሏል።
የአዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ ተጠቃሚዎች አንዳንዴ አገልግሎቱን ለማግኘት በአሽከርካሪዎች እንዲሁም በትኬት ቆራጭ ፈቃደኝነት ላይ ተመስርተን ነው የምንገለገለው የሚል ቅሬታ ያነሳሉና ድርጅቱ አሽከርካሪዎቹ መስመራቸውን በአግባቡ ስለመሸፈናቸው ተጠቃሚዎችን አለማንገላታታቸውን እንዴት ይቆጣጠራል ስንል በድርጅቱ የአገልግሎት ዘርፍ ድጋፍ ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ እንዳልካቸው ከበደ ጠይቀናል።

አሽከርካሪ የተመደበበትን መስመር መቀየር አይችልም ስለዚህ የተመደበበት መስመር አለ ያንን መስመሮችን ተከትለን አንቆጣጠራለን በተጨማሪ በአውቶቡሶቹ ላይ ዘመናዊ መቆጣጠሪያ ጂፒኤስ በመግጠም በሰአታቸው እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
ድርጅቱ ምንም ዓይነት የታሪፍ ማሻሻያ አለማድረጉን የነገሩን አቶ እንዳልካቸው በተጠቃሚዎች ፍላጎት የተራዘመ ተጨማሪ ጉዞ ሲኖር ነው የዋጋ ልዩነት እየመጣ ያለው ብለዋል።
በሌላ በኩል ድርጅቱ አዳዲስ የተመሰረቱ መንደሮችና የመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ያለን የትራንስፖርት እጥረት ለማሻሻል የመጠበቂያ ሰዓቱን በማሳጠር እንዲሁም የምልልስ መጠኑን በመጨመር የማሻሻያ ስራ እየሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያለው ማንኛውም ተገልጋይም በተቋሙ የአጭር ቁጥር 8981 በመደወል አቤቱታ ማቅረብ ይችላል አሁንም የሚደረጉ የአገልግሎት ማሻሻያዎችም እየተጨመሩ ይሄዳሉ ብሏል፡፡
ምህረት ስዩም








