በቀን እስከ 50 ሺህ ስኩዌር ሜትር ወይም ከ40 እስከ 45 ኮንቴነር ሴራሚክ ማምረት የሚችል ፋብሪካ ከ3 ሳምንት በኋላ ምርት ይጀምራል ተባለ።
- 5 hours ago
- 1 min read
መጋቢት 28/2018
በቀን እስከ 50 ሺህ ስኩዌር ሜትር ወይም ከ40 እስከ 45 ኮንቴነር ሴራሚክ ማምረት የሚችል ፋብሪካ ከ3 ሳምንት በኋላ ምርት ይጀምራል ተባለ።
በ50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኢንቨስትመንት ከአዲስ አበባ 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በቱለፋ ከተማ የተገነባው ይህን ፋብሪካ የገነባው ባይጂያ ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ የተባለ ድርጅት ነው።
በ30 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ የሴራሚክ እና የፖርስሊን ምርቶች ፋብሪካ ምርት ሲጀምር ብቻውን አሁን ካለው የሴራሚክ ፍላጎት እስከ 70 በመቶ ድረስ የማቅረብ አቅም አለው ተብሎለታል።

በባይጂያ ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ የሚመረቱን ምርቶች ለገበያ የሚያቀርበው ማንሰን ኢንቨስትመንትስ ነው።
የማንሰን ኢንቨስትመንትስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳዊት እርገቱ እና የባይጂያ ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ ዋና ስራ አስኪያጅ ጃንግ ሁዋ ይህኑን ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስመምነቱ ማንሰን ኢንቨስትመንትስ ለኢትዮጵያ ገበያ ተስማሚ የሆኑ እና በልዩ ሁኔታ ዲዛይን የተደረጉ የሴራሚክ እና የፖርስሊን ምርቶችን በባይጂያ ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ አማካኝነት በኢትዮጵያ ለማስመረት እና በብቸኝነት ለማከፋፈል ያስችለዋል ተብሏል፡፡
ባይጂያ ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ በበኩሉ ምርቶቹን በማንሰን ቴክኒካዊ ደረጃዎች፣ የምርት ስያሜ (ብራንድ) መስፈርቶች እና የገበያ ዝርዝር መመሪያዎች መሰረት ምርቶቹን የማምረት ኃላፊነት እንዳለበት ተነግሯል።
ስምምነቱ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጪ ምንዛሪ ፍሰትን በመቀነስ እና ጥራት ያላቸው የሴራሚክ ምርቶች በኢትዮጵያ እንዲመረቱ በማድረግ ሀገሪቱ የያዘቸውን የኢንዱስትሪ ልማት እቅድ ይደግፋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
ባይጂያ ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ የሚያመርታቸውን ሴራሚክስ እና ፖርስሊን ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ የተስማማው ማንሰን ኢንቨስትመንትስ አራዳ ሞል እና በብሔራዊ ቤተ መንግሥት የተነገባውን ምናብ ዌልነስ የሰራ ድርጅት መሆኑን ሰምተናል።
ንጋቱ ሙሉ





Comments