በመንግሥት አደረጃጀት እና ቅርፅ አጀንዳ ሥር ሲመክሩ የቆዩ የሥራ ቡድኖች ከ53 ንዑሳን ጉዳዮች ውስጥ በ50ው ላይ ተስማምተው ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ተሻግረዋል።
- 41 minutes ago
- 2 min read
በመንግሥት አደረጃጀት እና ቅርፅ አጀንዳ ሥር ሲመክሩ የቆዩ የሥራ ቡድኖች ከ53 ንዑሳን ጉዳዮች ውስጥ በ50ው ላይ ተስማምተው ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ተሻግረዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ተመካካሪ፤ ሦስት ንዑሳን አጀንዳዎች ግን ለአስማሚ ግብረ ኃይል ይላካሉ መባሉን ነግረውናል።
ወደ አስማሚ ግብረ ኃይል ይላካሉ ከተባሉት ንዑሳን አጀንዳዎች ውስጥ የመንግሥት ሥርዓቱ ፓርላሜንታዊ ሆኖ ከፓርላማ የሚመረጥ ፕሬዝዳንት ርዕሰ ብሔርም ርዕሰ መንግሥትም ሆኖ አገሪቱን ይመራት፤ ይህም በየስድስት ዓመቱ የሚካሄድ ሁለት የምርጫ ዘመን ይኑረው የሚለው አንዱ ነው።
ሙሉ ሥርዓቱ ፕሬዚዳንታዊ ይሁን እና ፕሬዚዳንቱ በቀጥታ ከሕዝብ ይመረጥ የሚለውም በዚህ ሥር የቀረበው ነው።
«የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ውክልና እንዴት ይሁን? ብሔሮች በምክር ቤቱ በአንድ ሚሊዮን አንድ ሰው የሚለው ነባር አሠራር ይቀጥል ወይስ ሁሉም ብሔሮች እኩል ውክልና ይኑራቸው?» የሚለው ሁለተኛው ወደ አስማሚ ግብረ ኃይል ይሄዳል የተባለ ጉዳይ መሆኑን ተሳታፊው አስረድተውናል።
ሌላ ተሳታፊ በበኩላቸው «የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመን ደግሞ 6 ዓመት ሆኖ እንዲገደብ እና ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ እንዳይችል በሕግ ይገደብ» በሚለው ላይ የሥራ ቡድኑ ተስማምቶ በቃለ ጉባኤ ላይ መፈረሙን ተናግረዋል።
ይህ ምክረ ሀሳብ የክልል መሪዎችን የሥልጣን ዘመንም ያካትታል።
በዚህ ምክረ ሐሳብ ሥር አንዳንድ ተመካካሪዎች የክልል መሪዎች የሥልጣን ገደብ ከአንድ የምርጫ ዘመን በላይ እንዳይሆን የሚል ሙግት ቢያቀርቡም፣ «ሁለት የምርጫ ዘመን» የሚለው ሐሳብ ማለፉን ጠቁመዋል።
ለምክክር ከቀረቡት ስምንት አጀንዳዎች ውስጥ በአራቱ ቡድን ተመካካሪዎች መስማማታቸውን የምክክር ኮሚሽኑ ተናግሯል ።
በአዲስ አበባ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ውይይት፣ የሥራ ቡድን ተመካካሪዎች ተስማምተው በቃለ ጉባኤ ላይ መፈረም የጀመሩት በትናንትናው ዕለት ነው።
በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ እየመከረ ያለው ቡድን ግን ጉዳዩ አከራካሪ ሆኖ በመቀጠሉ በዚህ ደረጃ ላይ አልደረሰም።
ይህ ቡድን «ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነው ሥርዓት የቱ ነው?» ለሚለው ጥያቄ አሐዳዊ፣ ፌደራላዊ እና ኮንፌደራል የሚሉ አማራጮች ቀርበውለት ነበር።
በዚህም አሐዳዊ እና ኮንፌደራል የሚሉት ምክረ ሐሳቦች በጥቃቅንና ንዑሳን ቡድኖች ደረጃ በተመካካሪዎች ቀርበው የነበሩ ቢሆንም፣ በአብዛኛው ተሳታፊ ስላልተደገፉ ከቡድን ውይይት ውጪ እንዲቀሩ መደረጉን ተመካካሪዎች ነግረውናል።
ከቀረቡት ሦስት አማራጮች ውስጥ «አሁን በሥራ ላይ ያለው የፌደራል ሥርዓት ይቀጥል» በሚለው ላይ መስማማታቸውን ጠቁመዋል።
በዚህ ርዕስ ሥር «ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፌደራል ሥርዓት ወይስ መልከዓ ምድርን?» የሚል አማራጭ ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ «መልከዓ ምድር» የሚለው አሁን ያሉትን ክልሎች እንዲፈርሱ ሊያደርግ ስለሚችል «ያለው ይቀጥል» የሚለው አብላጫ ድምፅ ማግኘቱን ከተሳታፊዎቹ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።
«አሁን ያለው የፌደራሊዝም ዓይነት በርካታ ችግሮች አሉበት» ያሉት ተመካካሪዎቹ፣ የተለዩት ችግሮች ተፈተው እንዲቀጥል መግባባት መፈጠሩን አስረድተዋል ።
በዚህ ርዕስ ጉዳይ ሥር የመከረው የተመካካሪዎች ቡድን «ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ይቋቋም» በሚለው ላይም መስማማቱ ተነግሯል።
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ሂደቱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ 500 አባላት ያሏቸው የሥራ ቡድኖች በአጀንዳዎቹ ላይ ከተስማሙ በኋላ ቀጣዩ ሂደት እያንዳንዱ ቡድን በሰባቱም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ገልጾ ነበር።
እስከ አሁን በመንግሥት አደረጃጀት፣ በሰላም ግንባታ፣ በሃይማኖት ጉዳዮች፣ በሙስና እና በመልካም አስተዳደር አጀንዳዎች ላይ የተወያዩ ተመካካሪዎች በሥራ ቡድን ደረጃ የምክረ ሐሳባቸውን ቃለ ጉባኤ ያጸደቁ ናቸው። ያሬድ እንዳሻው
_edited.jpg)



Comments