በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሰሜኑ ጦርነት ስጋት አድሮባቸው ስራ አቁመው የቆዩ ባለሃብቶች ዳግም ወደ ማምረት ለመመለስ ፍቃደኝነታቸውን እያሳዩ ነው ተባለ
- sheger1021fm
- 2 days ago
- 2 min read
ጥር 19/2018
በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ የነበሩ እና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ስጋት አድሮባቸው ስራ አቁመው የቆዩ ባለሃብቶች ዳግም ወደ ማምረት ለመመለስ ፍቃደኝነታቸውን እያሳዩ ነው ተባለ።
መንግስትም መሰረተ ልማቶችን መልሶ ሊያሟላላቸው እና የተለያዩ ማበረታቻዎችን ሊሰጣቸው እንደተስማማ ሠምተናል። በአሁኑ ወቅት በኢነዱስሪ ፓርኩ እየሰራ ያለው አንድ ባለሃብት ብቻ ነው ተብሏል፡፡
ለሁለት ዓመት ያህል በቆየው የሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ስራ አቁሞ የቆየው የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዳግም ወደ ማምረት እንዲመለስ ከአራት ወር በፊት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
ግብረ ሃይሉ በፓርኩ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ እና በጦርነቱ ምክንያት ለቀው የሄዱ ባለሃብቶችን በኢንተርኔትና ሌሎች አማራጮች አግኝቶ ማነጋገሩን፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ጳውሎስ በለጠ ነግረውናል።

ውይይቱን ተከትሎ በርካታ ባለሃብቶች ተመልሰው በፓርኩ ለመስራት ፍቃደኛ እንደሆኑ አሳውቀዋል ያሉን አቶ ጳውሎስ ፤ አንዳንዶቹም ትተዋቸው የሄዱ የማምረቻ ማሽኖቻቸው ያሉበትን ሁኔታ በአካል ተገኝተው እንደተመለከቱና - ጥገናም እንዳደረጉላቸው ጠቅሰዋል።
ነባሮቹ ብቻ ሳይሆኑ አዳዲስ ባለሃብቶችም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ገብተው ለመስራት ጥያቄ ማቅረባቸውን አቶ ጳውሎስ ነግረውናል። አሁን ላይ ጥያቄያቸው እየታየ ነው ብለዋል።
ነባሮቹ ባለሃብቶች እንዲመለሱ ፤ተጨማሪዎችም እንዲገቡ በልዩ ሁኔታ እንዲሰጡ የተወሰኑ ማበረታቻዎች እንዳሉም ሠምተናል።
በካሬ ሜትር የሚጠየቀውን የኪራይ ክፍያ መቀነስ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በብር ክፍያ እንዲፈጽሙ ማድረግ ከማበረታቻዎቹ መካከል እንደሆኑ አቶ ጳውሎስ ነግረውናል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ በመንግስት መሟላት ያለባቸው መሰረተ ልማቶችም እየተገነቡ ነው ተብሏል
የነበረውን ጦርነት ሰግተው የወጡ ባለሃብቶች፣ ማሽኖቻቸውን ከአገር ለማስወጣት ጥያቄ እንዳቀረቡ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም መናገሩ ይታወሳል።
እንደ አማራጭ ማሽኖቹን ከሚያስወጡ በአገር ውስጥ ወደ ሌላ አካባቢ በማዘዋወር እንዲሰሩ ጥያቄ እንዳቀረበም ኮርፖሬሽኑ ከወራት በፊት ገልጾ ነበር።
ማሽኖቹን ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ነቅለው እንዲወጡ መወሰን በራሱም አስቸጋሪ ያሉበት እንደሆነ ደግሞ አቶ ጳውሎስ ተናግረዋል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://url-shortener.me/2DUB
Instagram: https://url-shortener.me/2DUD












Comments