በ12 ባለሃብቶች ከንጋት ሃይቅ 3.8 ሚሊዮን ኪሎ ግራም አሳ መመረቱ ተነገረ፡፡
- 3 hours ago
- 2 min read
የካቲት 16/2018
በ12 ባለሃብቶች ከንጋት ሃይቅ 3.8 ሚሊዮን ኪሎ ግራም አሳ መመረቱ ተነገረ፡፡
በሃይቁ ካለው ከፍተኛ የአሳ ምርት አንፃር አሁንም ቢሆን በበቂ መጠን እየተመረተ አይደለም ተብሏል። ተጨማሪ ባለሃብቶች ወደ ስራው እንዲገቡም ጥሪ ቀርቧል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ በፈጠረውና ንጋት በሚል ስያሜ በሚጠራው ሰው ሰራሽ ሃይቅ የሚድሮክ ኤትዮጵያ አካል የሆነው ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪን ጨምሮ 12 ባለሃብቶች ከጉባ አካባቢ ወጣቶች ጋር በመሆን በዚህ ዓመት 3ሺህ 895 ቶን ወይም 3.8 ሚሊዮን ኪሎ ግራም አሳ አምርተው ለገበያ ማቅረባቸውን ሰምተናል፡፡
ባለሃብቶቹ ለአሳ ምርት አስፈላጊ የሆኑ የማስገሪያ ማሽነሪዎችንና ምርቱን ለማጓጓዝ የሚሆኑ ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎችን በማቅረብ ወደ ስራው መግባታቸውን ግድቡ የሚገኝበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የአሳ ሃብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ቡሼን ቡፋ ነግረውናል፡፡

ከዚህ ቀደም በክልሉ የነበረው የፀጥታ ችግር ለስራው እንቅፋት እንደነበር ያነሱት አቶ ቡሼን አሁን ይህ ችግር ተቀርፏል፤ ክልሉ ሰላማዊ ነው ብለዋል።
ይሁንና አሁንም ድረስ በቀጠለው የማስገሪያ ግብዓቶች እጥረት ምክንያት ለአሳ ማስገር ስራ ከተደራጁት 80 ማህበራት ወደ ስራ የገቡት 35 ብቻ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የማስገሪያ ግብዓቶች እንዲሟሉልን ለግብርና ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርበን የተወሰነ ድጋፍ አግኝተናል ግን በቂ አይደለም፤ ጀልባዎችን፣ መረብና ሌላውንም ለማሟላት ከረጂ ተቋማት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል፡፡
በንጋት ሐይቅ 29 የዓሣ ዝርያዎች እንዳሉና ፤ አሁን በብዛት ለገበያ እየቀረቡ ያሉት ሦስት ዓይነት ዝርያዎች ማለትም ቆሮሶ፤ ናይል ፐርችና አምባዛ ናቸው።

በበጀት ዓመቱ 9 ሺህ 995 ቶን ዓሣ ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፤ እስካሁን 3 ሺህ 895 ቶን ወይም 3.8 ሚኒዮን ኪሎ ግራም የዓሳ ተመርቷል፤
ይሁንና ከዓመቱ እቅድ አንፃር በመንፈቅ ዓመቱ የተመረተው አነስ ያለበትን ምክንያት አቶ ቡሼን ወቅቱ ለአሳ ምርት አመቺ ባለመሆኑ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በንጋት ሃይቅ ያለው አሳን የማምረት አቅም አሁን እየተመረተ ካለው በብዙ እጥፍ የበለጠ በመሆኑ ባለሃብቶች በርከት ብለው እንዲገቡ ይፈለጋል፤

በዚህ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ በመምጣት በአሳ ሃብት ልማት ላይ እንዲሰማሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የአሳ ሃብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ቡሼን ቡፋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በክልሉ ያሉ 5 ወንዞች በዓመት 2ሺህ 400 ቶን ወይም 2.8ሚሊዮን ኪሎ ግራም አሳ የማምረት አቅም አላቸው ተብሏል፡፡
የንጋት ሃይቅ ዓመታዊ የማመምረት አቅም 15 ሺህ ቶን ወይም 13.6ሚሊዮን ኪሎ ግራም መሆኑንም ከሃላፊው ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ……
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments