ሰኔ 5 2017 - በስራቸው ጠባይ ምክንያት ለአእምሮ ቁስለት የሚዳረጉ ጋዜጠኞች እንዳሉ ተጠቆመ
- sheger1021fm
- Jun 12
- 1 min read

ለአእምሮ የሚከብዱ ዘገባዎችን የሚሰሩ በተለይም ጦርነቶችን የሚዘግቡ፣የአእምሮ ጤና ተጎጂዎችን፣የአስገድዶ መድፈር እንዲሁም ከባድ የወንጀል ዘገባዎችን የሚሰሩ ጋዜጠኞች ለዚህ ሰለባ ናቸው ተብሏል፡፡
በባለሙያዎቹ አጠራር የአእምሮ ቁስለት(psychological trauma) ሚከሰተው ሰዎች እዕምሮን የሚያውኩ ከባድ ችግሮችን ካሳለፉ በኋላ ወይም በዚህ ስቃይ ውስጥ ያለፈን ግለሰብ ስሜት ሜት ሲጋባባቸው ነው፡፡
ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ባለሙያዎቹም ይሁኑ አሰሪዎቻቸው በስራቸው ምክንያት ሊገጥማቸው የሚችል የአዕምሮ ቁስለት እንደሚኖር አለመረዳታቸው እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ ይህ የተባለው ጋዜጠኞች በዚህ መንገድ ከሚመጣው የአእምሮ ቁስለት እራሳቸውን እየጠበቁ፤ለስራቸው ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን የሚሰጧቸውን ሰዎችም የአእምሮ ጤና ጠብቀው መስራት እንዲችሉ የሚያግዝ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር ይፋ በተደረገበት ወቅት ነው፡፡
ማህበሩ ከከተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለአንድ ዓመት የሚሰራበት ሲሆን የጋዜጠኛውን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ የነገሩን በፕሮጀክቱ ትግበራ ተሳታፊና የማህበሩ አባል የሆኑት መሰረት ከበደ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል በጦርነት ዘገባ ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች የአዕምሮ ቁስለት ተጠቂ ሆነው ተገኝተዋል የሚሉት ወ/ሮ መሰረት ጤንነታቸውን ጠብቀው ስለማይሰሩ ያሳለፏቸው ችግሮች ጠባሳ ትነው ያልፋሉ፤ፕሮጀክቱም ይህንን ክፍተት ለመሙላት ያለመ ነው ብለውናል፡፡
ከዚህም ባሻገር የጋዜጠኝነት ሙያ በጊዜ የተገደበ በመሆኑ ስራው የሚፈትረው ጥድፊያ በራሱ መፈተሸ ካልተቻለ የአእምሮ መቃወስ ሊፈጥር የሚችል ነው፤ይህንንም በመረዳት የሚዲያ ተቋማት የሚመሩባቸው ኤዲቶሪያል ፖሊሲዎች ይዘት ላይ የሚጨነቁትን ያህል የባለሙያውን ሁለንተናዊ ደህንነት ሊያካትቱ እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡በፕሮጀክቱ ለሚዲያ ባለሙያዎች የተዘጋጁ ስልጠናዎችን የሚሰጠው የኢትዮጵያ የአእምሮ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር በበኩሉ የአእምሮ ጤና ጉዳይ የሚዘገብበት መንገድ ችግር ያለበት፤የአእምሮ እክል ተጠቂዎችን ችግሮች የሚያባብሱ መሆናቸውን የነገሩን የማህሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አዜብ አሳምነው ናቸው፡፡
የአእምሮ ህመም ተጠቂዎች ብቻ ሳይሆኑ የህክምና ባለሙያዎችም በማህበረሰቡ መገለል ይደርስብናል የሚሉት ባለሙያዋ መሰል ፕሮጀክቶች ግንዛቤ የመፍጠር አቅም እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል፡፡በኢትዮጵያ ያሉ የስነ አዕምሮ ሃኪሞች 150 ብቻ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ምንታምር ፀጋው








