ሰኔ 25 2017 - አዋሽ ባንክ ከግብር በፊት 22 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን ተናገረ
- sheger1021fm
- Jul 2
- 1 min read
አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ያልተጣራ ትርፍ፤ ከግብር በፊት 22 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን ተናገረ፡፡
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የ12 ቢሊዮን ብር(113 በመቶ) ዕድገት አሳይቷል ብሏል፡፡
በሂሳብ ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ካፒታሉ አምና ከነበረበት የ10 ቢሊዮን ብር(37 በመቶ) እድገት በማስመዝገብ 37 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል ሲል አስረድቷል።
ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ ለተለያዩ የግብር ዓይነቶች በአጠቃላይ ከ10.8 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍያለሁ ብሏል፡፡
አዋሽ ብንክ በሁሉም ዋና ዋና የባንክ የስራ አፈጻጸም መለኪያዎች አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ሂሳብ ዓመቱን በጥሩ ውጤት አጠናቅቄያለሁ ሲልም አስረድቷል።
ባንኩ በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት (እ.ኤ.አ ሰኔ 30) ጠቅላላ ገቢ ከ64 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኖ መመዝገቡን የተናገረ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ28 ቢሊዮን ብር(77 በመቶ) ዕድገት አስመዝግቧል ብሏል።
አዋሽ ባንክ የተቀማጭ ሂሳብ መጠኑን በዘንድሮ ዓመት ብቻ ከ106 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ አጠቃላይ የተቀማጭ ሂሣብ መጠኑን 332 ቢሊዮን ብር ማድረሱን ተጠቅሷል፡፡

ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የብድር ጣርያ መሠረት የ20 በመቶ እድገት በማሳየት ከብር ከ219 ቢሊዮን በላይ ማድረስ ችያለሁ ብሏል።
ከዚህ የብድር መጠን ውስጥ በሂሳብ ዓመቱ ከ 16.6 ቢሊዮን ብር በላይ የተሰጠው በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለታቀፉ ከ14,000 በላይ ደንበኞች መሆኑ ተነግሯል፡፡
ከ301,000 በላይ ለሆኑ ደንበኞች ደግሞ ያለ ምንም ማስያዣ የዲጂታል የብድር አገልግሎት ከ493 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠቱ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
የባንኩ ተመላሽነታቸው አጠራጣሪ የሆኑ ብድሮች ምጣኔ በሂሳብ ዓመቱ 1.8 በመቶ መሆኑን አስረድቷል፡፡
አዋሽ ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስመዝገቡንም አስረድቷል፡፡
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ355 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር (25 በመቶ) ዕድገት አሳይቷል ብሏል፡፡
በአጠቃላይየቅርንጫፎቹን ብዛት 989፣ የደንበኞች ቁጥር ደግሞ ከ15 ሚሊዮን በላይ መድረሳቸውም ተነግሯል፡፡
ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ ውስጥ ለማህበራዊ ኃላፊነት ግዴታው ለመወጣት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም በዓመታዊ ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡
ንጋቱ ሙሉ












Comments