ሰኔ 25 2017 - በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ከፍታማ በሆኑ አካባቢዎች ከሚኖሩ ሰዎች 35 ሚሊዮን ያህሉ የሐሩራማ በሽታዎች ስጋት እንዳለባቸው ተነገረ፡፡
- sheger1021fm
- 1 day ago
- 2 min read
በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ከፍታማ በሆኑ አካባቢዎች ከሚኖሩ ሰዎች 35 ሚሊዮን ያህሉ የሐሩራማ በሽታዎች ስጋት እንዳለባቸው ተነገረ፡፡
ሃሩራማ በሽታዎች ከሚባሉት ውስጥ በተለይ ተላላፊ ያልሆነ የዝሆኔ በሽታ( #Podoconiosis )፤ ከፍታማ በሆኑና በግብርና ስራ ላይ በተሰማሩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ትልቅ የህብረተሰብ የጤና ስጋት መሆኑ ተነግሯል፡፡
በጉዳዩ ላይ የሚሰራው ማላሪያ ኮንሰርቴይም የተባለ ድርጅት ህመሙን ለመከላከል እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸዉን ሰዎች የሚያግዝ ሀፒ ፊት የተባለ ፕሮጀክት ቀርጾ የሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ድርጅቱ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ካላቸው ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና በጉዳዩ ላይ ጥናት ካደረጉት ተቋማት ጋር አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

ችግሩን ከመሠረቱ መከላከል ላይ በደንብ ካልተሰራበትም በተለይ የችግሩ ተጠቂዎች በአብዛኛው በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በመሆናቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሚያስከትል ነው ተብሏል፡፡
በሽታው የሚከሰተው በዋናነት ከአፈር ጋር በተያያዘ መሆኑንና በተለይ ከፍታ ቦታዎች ቀይ አፈር ያለባቸው አካባቢዎች ያሉት ሚኒራሎች በባዶ እግር ከተረገጡ ወደ ውስጥ በመግባት የጤና ስርዓትን በማዛባት በጊዜ ሂደት እና የእግር እብጠት እንዲያስከትል ያደርጋል የሚሉት በማላሪያ ኮንሰርቲየም ድርጅት (የፖዶኮኖሲስ) ወይም ዝሆኔ በሽታ መከላከል ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ኃላፊ የሆኑት አቶ እሰይ ባቲሶ ናቸው፡፡
በሽታው ከመከሰቱ በፊት መከላከል ላይ መስራት ትልቅ ለውጥ ያመጣል የሚሉት አቶ እሰይ ከተከሰተ በኋላ ግን ለህክምና የሚጠይቀው ጊዜ የረዘመ በመሆኑ በሽታውንም በቀላሉ ጫማ በማድረግ ብቻ መከላከል ላይ ለመስራት ፕሮጀክቱ ያግዛል ብለዋል፡፡

ህመሙ ከጤና ችግርነት ባለፈም በኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ጫና ከፍተኛ መሆኑን በተሰራ ጥናት አረጋግጠናል የሚሉት ደግሞ የናሽናል ፖዶኮኖሲስ አክሽን ኔትወርክ (ናፓን) የተባለ ኮንሰርቴይም ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቅሬ ኃይለ ኪሮስ ናቸው፡፡
በግብርና ስራ የሚተዳደሩና ችግሩ ያገኛቸው ሰዎች በዚህ በሽታ ምክንያት ወደ ስራ አይሄዱም፤ጥ ናቱ እንደሚያሳየው እንደውም ከጤነኞች ጋር ሲነጻጸር ምርታማነታቸው በሁለት እጥፍ ይቀንሳል ብለዋል፡፡
አርሰው መብላት አለመቻላቸው እንዲሁም የተለያዩ የኢኮኖሚ ስራዎቻቸው ሰርተው ከመምጣት አንጻር ውስንነት ይኖራቸዋልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ችግሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ስፋት ከፍተኛ ነውና አጠቃላይ መከላከል እንዲሁም የህክምና ስራው ላይ ምን እየተሰራ ነው ስንል በጤና ሚኒስቴር ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች መከላከል ቡድን መሪ የሆኑትን አቶ ተስፋሁን ቢሻውን ጠይቀናል፡፡
ለመከላከልና ኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በፊት ጀምሮ እየሰራች ነው አንደኛ መከላከሉ ላይ በተለይ ቀይ አፈር ያለባቸው ወረዳ አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ጫማ እንዲያደርጉ ማድረግና በጤና ፕሮግራምና በሌሎችም የጤና ትምህርት ላይ በማካተት እየተሰራ ነው ተደራሽነቱ ግን ያን ያህል ከፍተኛ አይደለም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ 1.5 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በሽታው ያለባቸው ሲሆን ሌሎች 35 ሚሊዮን ያህል ደግሞ የተጋላጭነት ስጋት ያለባቸው እንደሆኑ የተሰራ ጥናት ያሳያል፡፡
ኦሮሚያ፣ አማራና በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ስርጭት እንደሚታይም ሰምተናል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comentarios