top of page

ሰኔ 20 2017 - የእስራኤልና ኢራን ግጭት፣ በኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ምንድን ነው?

  • sheger1021fm
  • 5 hours ago
  • 2 min read

ባለሞያዎች ግጭቱ በንግግር መፍትሄን ካላገኘና የተራዘመ ከሆነ በዚህ ተጎጂ ከሚሆኑ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ልትሆን ትችላለች ይላሉ።


ዓለም የሀገራትን ንግድና ኢኮኖሚ ለረበሸው፣ የሩሲያ እና ዩክሬይን ጦርነት መቋጫ ሳታበጅ የኢራንና እስራኤል ግጭት ተከትሏል።


ቀጥተኛ የተኩስ ልውውጡ ከሰሞኑ በስምምነት ጋብ ቢልም፣ በአካባቢው ያለው ውጥረትና ስጋት ግን ባለበት ነው።


ልክ እንደተቀረው አለም ሁሉ፣ የሩስያ እና ዩክሬይን ጦርነት ብዙ ምርቶችን ከዚያ የምትሸምተውን የኢትዮጵያ ገበያም መረበሹን ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲያነሱ ይሰማል።


አሁን ውጥረት ውስጥ የገባው የመካከለኛው ምስራቅ አከባቢም፣ ከነዳጅ ባለፈ የኢትዮጵያ ብዙ ምርቶች መዳረሻ መሆኑን የሚያነሱት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ የሆኑት ዳርስከዳር ታዬ(ዶ/ር) ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያን ጨምሮ የተቀረውን ዓለም ሁሉ የጎዳው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት መቋጫ ሳያገኝ የኢራንና እስራኤል ውጥረት መከተሉ በዓለም ዙሪያ ያለውን የንግድ ልውውጥ የበለጠ የሚረብሽ ነው። በዚህ ተጎጂ ከሚሆኑት ቀዳሚ ሀገራት ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያም አለችበት ብለዋል።

እስራኤል እና ኢራን አሁን የደረሱበት ከመድረሳቸው በፊት፣ ባለፉት ጊዜያት ውጥረቱ ከቦታ ቦታ እየታየ አድማሱንም እያሰፋ እንደነበር የሚያነሱ ደግሞ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የመካከለኛው ምስራቅ ተመራማሪው መሀመድ ሰይድ(ዶ/ር) ናቸው።


ውጥረቱ ሊባኖስ፣ ሶሪያ እያለ ከዛም ቀይ ባህር እና የፋርስ ባህረ ሰላጤ እየተስፋፋ መምጣቱን ያነሳሉ ተመራማሪው። አካባቢው የንግድና የነዳጅ መተላለፊያ መሆኑ ጉዳዩን የሁሉም ሀገራት ያደርገዋል ብለዋል።


ኢትዮጵያ ደግሞ ከዚያ በዘለለ ለጉዳዩ ቅርብ እንድትሆን የሚያደርጋት ከንግድ ጋር በተገናኘ በአካባቢው ያላት ጥቅም ነው ሲሉ ያብራራሉ።


ለኢትዮጵያ ይህ አካባቢ መውጫ መግቢያ እስትንፋሷ መሆኑን በመግለፅ ከ95% በላይ ምርቷ የሚተላለፈው በዚህ መስመር ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ የምታስገባው ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውጪ ከምትልከው ምርትም አንድ ሶስተኛው ገደማ መዳረሻው ወደዚሁ አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል።


የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ 28 በመቶ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ መዳረሻ ሀገራት መሆናቸውን አብራርተዋል።


በእነዚህ እና በሌሎችም ምክንያቶች፣ በዚህ አካባቢ የሚፈጠር ቀውስ ለኢትዮጵያ ትልቅ ችግርን ይዞ የሚመጣ ይሆናል ብለዋል።


ቴዎድሮስ ወርቁ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page