ሰኔ 20 2017 - ኡጋንዳን በግንቦት ወር በነበረኝ አፈፃፀም ኢትዮጵያን በልጬ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቡና ላኪ የሆነኩበት ነው ብላለች
- sheger1021fm
- 4 minutes ago
- 2 min read
ለአለም ገበያ የቡና ምርት ከሚያቀርቡ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሁና ብትቆይም አሁን ተገዳዳሪ እየመጣባት ይመስላል፡፡
ኡጋንዳን በግንቦት ወር በነበረኝ አፈፃፀም ኢትዮጵያን በልጬ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቡና ላኪ የሆነኩበት ነው ብላለች፡፡
ኡጋንዳ ኢትዮጵያን በመብለጥ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ቡና ላኪ ሆናለች ሲል የሀገሪቱ የግብርና ፤ የእንስሳት እና አሣ ሃብት ልማት ሚኒስቴር ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መረጃ ይፋ አድርጓል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኡጋንዳ በአፍሪካ ቁጥር አንድ ቡና ላኪ ሀገር ሆነች ያለው ባለፈው ግንቦት ወር የነበራትን አፈጻጸም መነሻ በማድረግ ነው።
*ይህ ታሪካዊ ለውጥ በአህጉሪቱ የቡና ንግድ አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን ያሳያል*ም ብሏል፤ የኡጋንዳ የግብርና ፤ የእንስሳት እና አሣ ሃብት ልማት ሚኒስቴር።
ኡጋንዳ በግንቦት ወር 47,606 ቶን ቡና ለአለም ገበያ በማቅረብ ከ243 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማግኘቷ ተነግሯል።
ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ወደ ውጪ የላከችው ቡና 43,481 ቶን እንደሆነ የቡናና ሻይ ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል።
የዘንድሮው በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ አንድ ወር ተኩል እየቀረው ወደ ውጪ ከተላከ ቡና የተገኘው አጠቃላይ ገቢ ሁለት ቢለየን ዶላር መድረሱንም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከቀናት በፊት ይፋ አድርጓል።
የኡጋንዳ በቡና ንግድ ከአፍሪካ አንደኛ ሆኛለሁ ማለት ለኢትዮጵያ ደንገጥ የሚያደርግ ነገር አይኖረው ይሆን? ጥያቄውን ያቀረብንላቸው *የኢትዮጵያ ቡና ማህበር* ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ የለውም ባይ ናቸው።
ሁለቱም ሀገራት በአጠቃላይ አመቱን በሙሉ ለዓለም ገበያ ያቀረቡት ቡና ቢታይ ቀዳሚዋ አሁንም ኢትዮጵያ ስለመሆኗ ነው አቶ ግዛት የሚናገሩት።
የአንድ ወር የቡና ሽያጭ በተለያየ ምክንያት ከፍ እና ዝቅ ሊል እንደሚችል የሚናገሩት አቶ ግዛት ይሄ በዓለም ላይ ትልቋ ቡና አምራች እና አቅራቢ በሆነችው ብራዚል ላይ ጭምር እንደሚታይ ጠቅሰዋል።
የተከታታይ ወራት መቀነስ ካለ ግን ምንድነው የተፈጠረው ብሎ መጠየቅ ይገባል ብለዋል።
ኡጋንዳ የቡና ምርት ላይ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች እንደምትገኝ ግን መካድ እንደማይቻል ነው *የኢትዮጵያ ቡና ማህበር* ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ የሚጠቅሱት።
በሀገሪቱ ከሚመረተው ቡና አብዛኛው ለዓለም ገበያ የሚቀርብ እንደሆነ ጨምረው ነግረውናል።
ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ስፔይን፣ ህንድ፣ ሡዳን፣ ቤልጂየም፣ ቻይና፣ አልጄሪያ፣ አሜሪካና ሞሮኮ ከፍተኛዎቹ የኡጋንዳ ቡና ገዥ ሀገራት ናቸው።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments