top of page

ሰኔ 12 2017 124 የመንግስት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እየተሰጡ መሆኑን የሲቨል ሰርቪስ ኮሚሽን ተናገረ

  • sheger1021fm
  • 10 minutes ago
  • 2 min read

በአገልግሎት አሰጣጣቸው ተደጋግሞ በማህበረሰቡ ቅሬታ የሚነሳባቸው የመንግስት አገልግሎቶችን፤ ለአገልግሎት አሰጣጥ የተመቹና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥባቸው እንዲሆኑ ለማድረግ ስራዎች መጀመሩን ኮሚሽኑ ተናግሯል።


በዚህም ከወንኩት ባለው ሪፎርም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሚል የ23 የመንግስት ተቋማትን 124 አገልግሎቶች ቀልጣፋ አገልግሎቶች እንዲሰጥባቸው ለማስቻል ወደ አንድ ማዕከል ገብተዋል ብሏል።


ከ124ቱ አገልግሎች መካከል የፓስፖርት አገልግሎት፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ የሰነዶች ማረጋገጫና የንግድ ፍቃድ አገልግሎቶች እንደሚገኙበት ከኮሚሽኑ ሰምተናል።


ይህ የተባለው ከፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 14 እስከ ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ አዲስ አበባ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የምታስተናግደውን አለም አቀፍ ጉባኤ አስመልክቶ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መግለጫ በተሰጠበት ወቅት ነው።

ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫውን የሰጡት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሃይሌ(ዶ/ር) በጉባኤው ኢትዮጵያ አገልግሎቶችን ለማዘመን የሰራችውን ስራ አስመልክቶ ተሞክሮዎቿን ታቀርባለች ብለዋል።


ለ3 ቀናት በትዩ የሚካሄደው ጉባኤ የመጀመሪያው የአፍሪካ ህብረት አባላት ሀገራት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳድር 10ኛ ጉባዔ ሲሆን ሁለተኛው በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ቀጣናዊ ፎረም መሆኑ ተጠቅሷል፡፡


በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳድር ጉባዔ የመንግሥት ተቋማት ተለዋዋጭ ከባቢያዊ ሁኔታዎችን መቋቋምና ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በፍጥነት መቅረፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።


በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ቀጣናዊ ፎረምም በተመሳሳይ "የመንግሥት አገልገሎት አስተዳደርና ኢኖቬሽን" በሚል የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።


ይህንን መድረክ ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ የተመረጠችው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመጀመሯ መሆኑንም አንስተዋል፡፡


በብዙ ሃገራት ተሞክሮ ውጤት ያመጣው የአንድ ማዕከል አስፈላጊነት ላይ በትኩረት ውይይት ይደረጋል፤በየሃገራቱ የሚስፋፋበትና የሚፈፀምበት ሁኔታ ላይ የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት መሆኑም ተነግሯል፡፡


የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ዶ/ር መኩሪያ ሃይሌ በጉባኤው ኢትዮጵያ አገልግሎቶችን ለማዘመን ሰራሁ የምትለውንና ተሞክሮዎቿን ታቀርባለችም ብለዋል።


የአገልግሎት አሰጣጥ ለውጥ ሊመጣባቸው ይገባል የተባሉ የመንግስት ተቋማት በ3 ምዕራፍ ተከፍለው በመጀመሪያው ምዕራፍ 8 ሚኒስቴር መስሪያቤቶች በቅድመ ዝግጅት ስራ ላይ ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ ከሰኔ 30 2017ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገቡ ጠቅሰዋል፡፡


ተቋማቱ ጠንካራ አቅም ፈጥረው ለህዝቡ የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲያሻሽሉ ለማድረግ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እየሰራ ባለው ስራ እስካሁን 124 የመንግስት አገልግሎቶች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማስገባቱን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡


ከፌድራል ተቋማት በተጨማሪ በክልል ደረጃ ያሉ የመንግስት ተቋማት በዚህ ዓመት መጨረሻ ጀምረው ቢያንስ በየክልሉ አንድ አንድ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲኖራቸው ከክልሎች ጋር ስምምነት ላይ ደርሰን ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል፡፡


ከሰኔ 14 እስከ 16 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው አህጉር አቀፍና አለም አቀፍ ጉባኤ ከአፍሪካ፣ከመካከለኛው ምስራቅና ከእስያ የተወከሉ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ሰምተናል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page