top of page

ሰኔ 11 2017 - የተፈጥሮ ማዳበሪያ አምራቾች ኮምፖስትን ከመደበኛው የማዳበሪያ ዋጋ ከ10 እጥፍ በላይ ቀንሰው ለገበያ ቢያቀርቡም ገበያ አጣን እያሉ ነው

  • sheger1021fm
  • 4 hours ago
  • 2 min read

የተፈጥሮ ማዳበሪያ አምራቾች ኮምፖስትን ከመደበኛው የማዳበሪያ ዋጋ ከ10 እጥፍ በላይ ቀንሰው ለገበያ ቢያቀርቡም ገበያ አጣን እያሉ ነው፡፡


በአዲስ አበባ ለእርሻ ስራ የሚሆን የተፈጥሮ ማዳበሪያ(ኮምፖስት) የሚያመርቱ 58 ያህል አምራቾች አሉ፡፡


ከእነዚህ መካከል የሆነውና ጂቱ ኮምፖስት የተሰኘውን ማዳበሪያ እያመረተ ያለው የብሩክ ሰላዊት ጓደኞቻቸው የኮምፖስት ማምረት ህብረት ሽርክና ማህበር ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በዚህ ስራ ላይ ተሰማርቶ ኮምፖስት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ነግሮናል፡፡


የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከኬሚካል ማዳበሪያ አንጻር የአፈር ለምነትን የሚጠብቅ፤ ምርታማነትን የሚጨምር፤ በዋጋም ከ10 እጥፍ በላይ ቅናሽ ያለው መሆኑን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ፀሃይ ነግረውናል፡፡


ሁለቱን የሚያነፃፀሩት ስራ አስኪያጁ የኬሚካል ማዳበሪያዎች ከምርት ይልቅ የአፈሩን አሲዳማነት የሚጨምሩ ናቸው፤ የተፈጥሮው ማዳበሪያ ግን ገበሬው አንድ ጊዜ ከተጠቀመው እስከ 3 ዓመት ድረስ ማዳበሪያ መጠቀም የማያስፈልገው ነው ይላሉ፡፡


ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ሰዎች ያልገባቸውና ሊረዱት የሚገባው በሁለቱ ማዳበሪያዎች መካከል እጅግ የሰፋ የዋጋ ልዩነት እንዳለ ነው የሚሉት አቶ ብሩክ በአሁኑ ወቅት ዳፕና ዩሪያ የሚባለው የኬሚካል ማዳበሪያ የገበያ ዋጋው በኩንታል 12 ሺህ ብር ደርሷል፤የተፈጥሮው ማዳበሪያ ግን በኩንታል እስከ 1ሺህ ብር እንደሆነም ያነሳሉ፡፡


ገበያው በጣም ጠባብ በመሆኑ እነዚህ ሁሉ አምራቾች የማምረት አቅማቸውን ያህል እያመረቱ እንዳልሆነም ነግረውናል፡፡

ድርጅታቸውን እንደማሳያ የሚጠቅሱት አቶ ብሩክ ጂቱ ኮምፖሰት አልፎ አልፎ ለግለሰቦችና ድርጅቶች ከማቅረብ ውጪ አብዛኛውን ምርቱን የሚያቀርበው በአዲስ አበባ እየተሰሩ ላሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡


የተፈጥሮ ማዳበሪያ አምራቾች እንደልብ ገበሬው ጋር መድረስ ያልቻሉት የሎጂስቲክ ችግር ስላለባቸው ነውም ተብሏል፡፡


ይህንንም ሲያስረዱ አንድ ገበሬ በአንድ ሄክታር መሬቱ ላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ለመጠቀም ቢፈልግ በብዛት መጠቀም አለበት በአማካኝ ከ20 እስከ 30 ኩንታል ያስፈልገዋል፤ይህንን ከተጠቀመ በኋላ ግን እስከ 3 ዓመት ድረስ ሊያገለግል ይችላል፤ በመሆኑም የሚፈለገውን ያህል ምርት ገበሬው ያለበት ድረስ ለጓጓዝ የሚወጣው ወጪ አንዳንድ ጊዜ ከማዳበሪያው ዋጋ በላይ እየሆነብን ተቸግረናል፤የግብርና ሚኒስቴር በዚህ በኩል ያለውን የሎጂስቲክ ችግር እንድንቀርፍ ቢያግዘን ያሉትንም ነግረውናል፡፡


በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ለኮምፖስት ማዳበሪያ የሚሆን የተለየ የጥራት ማረጋገጫ (standard) ደረጃ የለም፤ይህም ቢዘጋጅ ብለዋል፡፡


ለአንድ ሄክታር መሬት በአማካኝ 5 የኬሚካል ማዳበሪያ ሲያስፈልግ ለግዢ እስከ 60,000 ብር ማውጣት ያስፈልጋል፡፡


በአንፃሩ ለአንድ ሄክታር መሬት እስከ 25 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪ መጠቀም ያስፈልጋል እስከ 25,000 ብር ወጪ ይጠይቃል፡፡


የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምንም አይነት ኬሚካል ሳይጨመርበት ከየቤቱ ከሚወጣ መበስበስ ከሚችል ውጋጅ ቆሻሻ የአሰራር ሂደቱን ጠብቆ የሚሰናዳ የማዳበሪያ አይነት ነው፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





コメント


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page