top of page

ሰኔ 10 2017 - በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን የሚመረምር ሰው፤ በምርመራ ወቅት ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት ከግድያ ውጪ የትኛውንም ዓይነት ወንጀል ቢፈጽም ተጠያቂ የማያደርግ አዋጅ ጸደቀ

  • sheger1021fm
  • 2 hours ago
  • 3 min read

በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን የሚመረምር ሰው፤ በምርመራ ወቅት ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት ከግድያ ውጪ የትኛውንም ዓይነት ወንጀል ቢፈጽም ተጠያቂ የማያደርግ አዋጅ ጸደቀ፡፡


በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ በህዝብ አንደራሴዎች ምክር ቤት ጸድቋል፡፡


አዋጁ በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ (Under cover investigation) እንዲያስፈጽም የተመደበ ሰው፤ በግዴታ ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያትና ከፈቃዱ ውጪ በሆኖ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም ይላል።

የምክር ቤት አባሉ አለሙ ጎንፋ(ዶ/ር) በአዋጁ 5/15 ላይ የቀረበው ዐረፍተ ነገር ትንሽ ከባድ መስሎ እንደታያቸው ተናግረው አዋጁ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡


እንደዚህ ዓይነት አዋጅ በተለይ ሽብርን ለመከላከል ለሀገራችን ያስፈልጋታል ሲሉ የምክር ቤት አባሉ ተናግረዋል፡፡


‘’የሆነው ሆኖ ግን አንድ ሰው በግዳጅ ላይ እያለ ከግድያ በስተቀር ለሚፈጽመው ወንጀል አይጠየቅም ይላል፡፡ አንደኛ ወንጀል ፈጽሟል ይላል፣ ወንጀል ፈጽሞ አለመጠየቅ ትክክለኛ አይመስለኝም፡፡ ወይም ድርጊቶቹ ተዘርዝረው ህጋዊ መብት የተሰጠው ሰው ሚወስዳቸው እርምጃዎች ወንጀል አይደሉም ብለን ማለፍ እንጂ አንድ ሰው በግዳጅ ላይ እያለ ለሚፈጽመው ወንጀል ከግድያ በስተቀር የሚለውን ሰው እንደፈለገ እንዲሆን የሚያደርግ ነው’’ ሲሉ አለሙ(ዶ/ር) ሃሳበቸውን አስረድተዋል፡፡


ሌላ ሙሉቀን አሰፋ የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው "እኔ በግሌ እንደተፎካካሪ የፖለቲካ ሰው አዋጁ ባለሀብቶችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና የታዋቂ ሰዎችን መብት የሚገድብ ነው" ብለዋል፡፡

"እንዲያውም የመናገር መብትን ይከለክላል የሚል እምነት ነው እኔ ያለኝ "ያሉት የምክር ቤት አባሉ ‘’ምክንያቱም አዋጁን ስናየው በ10 ዓመት ገድቦ ነው የወጣው’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡


‘’ህግ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው ተግባራዊ መደረግ ያለበት’’ ያሉት አቶ ሙሉቀን ‘’ስለዚህ ከ10 ዓመት ወዲህ ብሎ ማውጣቱ የተወሰኑ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ለማጥቃት ያሰበ ስለሆነ ለሀገራችንም ጥሩ አይደለም የሚል እምነት አለኝ’’ ብለዋል፡፡


‘’በአለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ እንደተገለጸው ሀይልን በመጠቀም፣ ንጹሃንን በማስገደድ አላማቸውን ለማስፈጽም የሚሳተፉ ተዋናዮችን ተጠያቂ ለማድረግ ሳይሆን አዋጁ እየዋለ ያለው በዋነኝነት የመንግስት ተቃዋሚዎችን፣ መንግስት ውስጥ ሆነው መንግስትን የሚተቹትን እና ጋዜጠኞችን ነው’’ ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ(ዶ/ር) ናቸው፡፡


‘’የአዋጁን ዝርዝር ካየንው በጣም አስገራሚ የሆኑ ድንጋጌዎችን ይዟል’’ ያሉት የምክር ቤት አባሉ ‘’ለምሳሌ የፋይናንስ ድህንነት አገልግሎት አጠራጣሪ ግብይትን ለ7 ቀን አግዶ ማቆየት ይችላል ይላል ያውም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ’’ ብለዋል፡፡


‘’አዋጁ በሽፋን ስር ምርመራ የሚያካሄድ መርማሪ ከግድያ ወንጀል ውጭ በሌላ ወንጀል አይጠየቅም ይላል’’ ያሉት ደሳለኝ ጫኔ(ዶ/ር) ‘’ለምሳሌ መርማሪው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ተደራድሮ ከሆነ ከወንጀለኛው ጋር መቀበሉን ብናውቅ አይጠየቅም ማለት ነው? ማሰቃየት ቢፈጽም፣ የመብት ጥሰት ቢፈጽም አይጠየቅም ማለት ነው? መሆን ያለበት ግን ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው አለም አቀፍ ድንጋጌዎች የተካተቱ ወንጀሎችን አለመፈጸሙ ነው’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ሌላው አቶ ዘካሪያስ የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ‘’አዋጁ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት እንደሚሉት ተቃዋሚን እና የሚዲያ ሰዎችን ለማፈን አይደለም’’ ብለዋል፡፡


አቶ ሳዲቅ አደም የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ‘’አዋጁ ጠንከር ያለ መሆኑን ተናግረው ጠንከር ያለበት ምክንያትም ግልጽ ነው’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ያለንበት ቀጠና አስቸጋሪ ነው፤ ሽብርተኝነት የሚበዛበት በመሆኑ የአዋጁ ከበድ ማለት ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከመብት አንፃር ሊታዩ የሚችሉ ነገሮች አሉ ያሉት አቶ ሳዲቅ ከህገ መንግስታችንም ስንነሳ ፍጹም የሚባል መብት የለም ብለዋል፡፡


‘’ከመብቶች ሁሉ የላቀ ዋና መብት የሚባለው በህይወት የመኖር መብት ነው ይህ መብትም ፍጹም አይደለም’’ ሲሉ የተናገሩት የምክር ቤት አባሉ ‘’ስለዚህ መብት የሚባለው ነገር ለህዝብ፣ ለማህበረሰብ እና ለሀገር ድህንነት ሲባል በየትኛውም ሀገር መብቶችን ፍጹማዊ አድርጎ የሚያስቀምጥ የለም’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡


‘’ስጋት አድርጎ የሚወስድ ወገን ሊኖር ይችላል ግን ለምን ይሰጋል?’’ ሲሉ የጠየቁት የምክር ቤት አባሉ ‘’ይህ አዋጅ ሲወጣ ለመጠርጠርም መሟላት ያለበት ነገር አለ ማንኛውም ወገን እነዚህ በአዋጁ የተቀመጡ ነገሮችን ካሟላ አይነካም ዋናው መስፈርቱን ማሟላት ነው’’ ብለዋል፡፡

‘’አዋጁ የወጣው በንድፍ ሃሳብ የምንፈራቸውን ለመከላከል ሳይሆን በተግባር እያየን እየኖርንበት ያለውን ነው’’ የሚሉት አቶ ሳደቅ ‘’ሽብርተኝነት በሀገራችን በስፋት አለ ኤ ቤ ሲ ብለን ልንጠራቸው የምንችላቸው ግለሰቦች እና ወገኖች አሉ ስለዚህ ይህን ለመከላከል ለምን እንሰጋለን’’ ብለዋል፡፡


የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሮ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ የሚደረገው ምርመራ ልዩ መሆኑን ተናግረው አዋጁ አንድን ቡድን ለማጥቃት ታስቦ የወጣ አይደለም ብለዋል፡፡


በመጨረሻም ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው በማሻሽያ ረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ በሶስት ተቃዉሞ በአንድ ድምጽ ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page